
የመስቀል በዓል በኢትዮጵያ በሁሉም አካባቢዎች በየዓመቱ በድምቀት የሚከበር በዓል ነው፡፡ በዓሉ በማይዳሰስ ዓለም አቀፍ ቅርስነትም የተመዘገበ ነው።
መስቀል ማኅበረሰቡ በጋራ ተሰባስቦ በዓደባባይ እና በየሰፈሩ የሚያከብረው ተወዳጅ በዓል ነው። ለበዓሉ ማድመቂያ እንደየ አካባቢው ባሕል የተለያዩ ባሕላዊ ምግብ እና መጠጦች ይዘጋጃሉ፡፡
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የመስቀል በዓል በድምቀት ከሚከበርባቸው ቦታዎች መካከል አንዱ ነው፡፡
አብዚ በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ለክብረ በዓል፣ ለድግስ እና ለተለያዩ ማኅበረሰባዊ ሁነቶች የሚዘጋጅ ባሕላዊ ምግብ ነው፡፡ በተለይም የመስቀል በዓል በጋራ በሚከበርበት ጊዜ ተዘጋጅቶ የሚቀርብ ምግብ ነው።
አብዚ የጤፍ እንጀራን በግብዓትነት በመጠቀም የሚዘጋጅ ምግብ ነው። አብዚ እንጀራውን በትኩስ በማነባበር ወይም በመደራረብ የተለያዩ ማባያዎችን በመቀባት ይዘጋጃል፡፡
አብዚ ብዙ ዓይነት ሲኾን በፍስክ ጊዜ የአይብ አብዚ እና የቅቤ አብዚ (ቅቤ በአዋዜ) ይዘጋጃል፡፡ የአይብ አብዚ አይቡን በተለያዩ ቅመሞች በመቀመም የሚዘጋጅ ነው። የቅቤ አብዚ ደግሞ በርበሬን የተለያዩ ቅመሞችን በመጠቀም ከለጋ ቅቤ ጋር በማዋሃድ የሚዘጋጅ ነው፡፡ በጾም ጊዜም በሽሮ፣ በክክ ወጥ፣ በአዋዜ እና በኑግ ተቀብቶ ይዘጋጃል፡፡
አብዚ በተለይም ለመስቀል በዓል ከዋዜማው ወይም ከደመራው ጀምሮ በዕለቱም ማኅበረሰቡ ተሰባስቦ በሚያከብርበት ጊዜ በዋናነት የሚቀርብ ምግብም ነው፡፡
ሁሉም የበዓሉ ተሳታፊዎች እንደየአቅማቸው በየቤታቸው ያለውን አብዚ አዘጋጅተው ይዘው በዓሉ በሚከበርበት ወይም ደመራ ወደ ተለኮሰበት ቦታ በመውሰድ ከባሕላዊ መጠጦች እንደ ጠላ፣ ጠጅ እና አረቂ ጋር ይቀርባል፡፡
አብዚ ከመስቀል በዓል በተጨማሪ በሌሎች ባሕላዊ ክብረ በዓላትም ይቀርባል፡፡ ባሕሉ ወደ ትውልድ እንዲሻገር በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የሚሠራው የማስተዋወቅ ሥራ እየተሠራ ይገኛል፡፡
አብዚን ማኅበረሰቡ ለራሱ ከመጠቀም ባለፈ ወደ ገበያ እንዲገባ በሆቴሎች እና ሬስቶራንቶች የምግብ ዝርዝር ውስጥ ተካትቶ እንግዶች እንዲጠቀሙት እየተደረገ ይገኛል።
ባሕልን መጠበቅ፣ ማልማት እና ለቱሪዝም ግብዓት እንዲውሉ ማድረግ ለማኅበረሰቡ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ከፍተኛ ነው፡፡ ባሕላዊ ምግብ እና መጠጦች ደግሞ የአንድ ማኅበረሰብ መገለጫ በመኾናቸው በአግባቡ ጠብቆ ለሌላው የማስተዋወቅ ተግባሩ አካል ሊኾን ይገባል።
#ባሕር_ዳር #መስከረም_15_2019_ዓ_ም
✍️ በፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
