የተራራው ላይ የመስቀል በዓል _ አንኮበር

6

 

አንኮበር በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ከደብረ ብርሃን ከተማ 42 ኪሎ ሜትር ገደማ ላይ የምትገኝ፣ ታሪክ፣ ባሕል እና ተፈጥሮ የተጣመሩባት ታሪካዊ ሥፍራ ናት። በቀደሙት ዘመናት የሸዋ ነገሥታት ማዕከልም ኾና አገልግላለች።

አንኮበር እና አካባቢዋ የአጼ ምኒልክ ቤተ መንግሥት፣ ጥንታዊ አብያተ ክርስትያናት፣ የወፍ ዋሻ ደን፣ የቀደምት የሸዋ ነገሥታት የቀብር ቦታ፣ ፍልፍል አብያተ ክርስትያናት የሚገኙበት ሁሉአቀፍ የቱሪዝም መዳረሻ ናት።

በአብያተ ክርስትያናትም በነገሥታቱ ዘመን ጀምሮ የነበሩ የብራና መጻሕፍት እና የታሪክ ንዋያተ ቅድሳት በውስጣቸው እንደሚገኙም ከአንኮበር ወረዳ ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ከእነዚህ የቱሪዝም ጸጋዎች በተጨማሪ የደመራ በዓልም በአንኮበር ከጥንት ጀምሮ በልዩ ኹኔታ ይከበራል።

የአንኮበር ወረዳ ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ጽሕፈት ቤት የቅርስ ጥበቃ እና ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ ዩሐንስ ንጋቴ እንደተናገሩት የደመራ በዓል አከባበር በአንኮበር ልዩ ታሪካዊ መነሻ አለው።

እንደ ባለሙያው ማብራሪያ ግማደ መስቀሉ ወደ ኢትዮጵያ በገባበት ወቅት ግሸን ደብረ ከርቤ ከመድረሱ በፊት በአንኮበር ሦሥት ቦታዎች ላይ አርፎ እንደነበር አብራርተዋል።

እነዚህም ቦታዎች በአንኮበር (የአጼ ምኒልክ ቤተ መንግሥት)፣ በደብደቦ መስቀለ ክርስቶስ ቤተ ክርስትያን እና በእመ ምሕረት ተራራ ላይ አርፏል።

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ደረጃ የደመራ በዓል ለመጀመሪያ ጊዜ በ1459 ዓ.ም የተከበረውም በዚሁ በአንኮበር ነው ብለዋል። ቀጥሎም በ1460 ዓ.ም በዚሁ ቦታ በእመ ምሕረት ተራራ ላይ መከበሩን አንስተዋል። በዚህ መክንያት የደመራ በዓል በአንኮበር ከሌሎቹ አካባቢዎች የተለየ እንደሚያደርገው አስረድተዋል።

የዘንድሮው በዓልም በአንኮበር (በአጼ ምኒልክ ቤተ መንግሥት) እና በእመ ምሕረት ተራራ ላይ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን እና ባሕላዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ እንደሚከበር ተናግረዋል። ለዚህም አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት።

#አሚኮ #Tourism #Ethiopia🇪🇹

#ባሕር_ዳር #መስከረም_15_2019_ዓ_ም

ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“ሁልጊዜም ከሕዝብ ጎን”