
የፈጣሪን የማያልቅ ጥበብ በአንድነት ለመመልከት፤ በተፈጥሮው አስደናቂነት እና ውበት ለመመሰጥ ለሚሹ የጉዞ አፍቃሪያን ሁሉ የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ወደር የማይገኝለት ቀዳሚ መዳረሻ ነው።
የኢትዮጵያ ጣራ የኾነው ይህ ድንቅ ሥፍራ የበጋው አቧራ በክረምቱ እርጥበት ሲረሰርስ ምድሩ በለምለም አረንጓዴ ምንጣፍ ይሸፈናል፤ ተራራዎች በተለየ የሕይወት እና የውበት መልክ ይገለጣሉ።
ክረምቱ አልፎ ጸደይ ሲተካ ዝናብ ሕይወት የዘራባቸው የጅንባር ፏፏቴ እና ሌሎች አያሌ ምንጮች ከተራራው ጫፍ እየተወረወሩ ወደ ጥልቁ ገደል ሲፈስሱ የሚፈጥሩት ድምፅ እና ትዕይንት የጎብኝዎችን ልብ በሀሴት ይሞላል።
ከዚህም በላይ እንደ ዋሊያ፣ ጭላዳ ዝንጀሮ እና ቀይ ቀበሮ ያሉ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ብርቅዬ የዱር እንስሳት ከአንዱ ተራራ ወደ ሌላኛው ተራራ በደስታ ሲቦርቁ መመልከት የትኛውም ጎብኝ መመልከት የሚፈልገው ትዕይንት ይኾናል።
በዚህ ወቅት በርካታ የውጭ ሀገር ጎብኝዎች የዚህን አስደናቂ የተፈጥሮ ድባብ ለመጋራት ባሕር ተሻግረው ይመጣሉ። በፓርኩ ውስጥ በሚኖራቸው ቆይታ በጀብዱ በተሞላ የእግር ጉዞ ድንቅ ጊዜን ያሳልፋሉ። ቅዝቃዜውን ተቋቁመው በተራራው ሰንሰለቶች መካከል በሚያደርጉት ጉዞ እያንዳንዱ እርምጃ የፓርኩን አስደናቂ ዕይታ ይገልጥላቸዋል።
በጭላዳ ዝንጀሮዎች መናህሪያ በለመለሙ ሳር ላይ ድንኳን ጥለው የሚያሳልፉት ምሽት ደግሞ ሌላው በዘመናቸው የማይረሱት የሕይወት ልምዳቸው ይኾናል።
ከፓርክ ውጭ ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር የሚደረጉ ጨዋታዎች፣ የሙዚቃ እና የታሪክ ልውውጦችም የባሕል ትስስርን እና ዘላለማዊ ወዳጅነትን በውስጣቸው ይቀርጻል።
ይህ የሰው እና የተፈጥሮ ተዓምራዊ መስተጋብር በወረርሽኝ እና በጦርነት ከነበረበት የቱሪስት መቀዝቀዝ ተላቅቆ አሁን ላይ በአዲስ ተስፋ ማንሰራራት ጀምሯል።
የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ የዱር እንስሳት ቱሪዝም ባለሙያ ላቀው መልካሙ እንደሚሉት የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ከዓለም አቀፉ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና በአካባቢው ተከስተው ከነበሩ አለመረጋጋቶች በፊት በዓመት እስከ 32 ሺህ የሚደርሱ የውጭ ሀገር ጎብኝዎችን በደስታ ያስተናግድ ነበር ብለዋል።
ባለፉት ሦሥት እና አራት ዓመታት በነበሩት ተደራራቢ ፈታኝ ምክንያቶችም የጎብኝዎች ቁጥር ቅናሽ አሳይቶ መቆየቱን አንስተዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአካባቢው የሰላም እና ደኅንነት ሁኔታ በአንጻራዊነት መሻሻል በማሳየቱ የቱሪዝም እንቅስቃሴው በጥሩ ሁኔታ እያገገመ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በዚህ መሠረት በ2018 ዓ.ም 5 ሺህ 370 የሚኾኑ ጎብኝዎች ፓርኩን እንደጎበኙ ገልጸዋል። በ2019 ዓ.ም ደግሞ የቱሪዝም እንቅስቃሴው መነቃቃት በከፍተኛ ደረጃ ጨምሮ ተስፋ እንደተጣለበት ነው የተናገሩት።
በዚህ ሂደት ይህንን ሥፍራ የረገጡ ጎብኝዎች ሁሉ ወደየሀገራቸው ሲመለሱ ይዘውት የሚሄዱት ሻንጣ እና ቁሳቁስ ብቻ ሳይኾን ከህሊናቸው የማይጠፋ ትልቅ የትውስታ ስንቅ እንደኾነም አንስተዋል።
በፓርኩ ውስጥ የጎብኝዎች ካሜራ የማያርፍበት ሥፍራ የለም። በካሜራቸው ያስቀሯቸው በጉም የተከበቡ የተራራ ጫፎች፤ በቀለማት ያሸበረቁ አበቦች”፤ የፓርኩ ድምቀት የኾኑ ብርቅየ እንሰሳት እና ሌሎች ውብ ምስሎች የሀገሪቱን መልካም ገጽታ በመገንባት ረገድ ህያው የዲፕሎማሲ ሚና ይጫወታሉ።
ለዚህም ነው ይህ የስሜን ተራራዎች ላይ የጎብኝዎች ቆይታ ለኢትዮጵያ ከኢኮኖሚ እስከ መልካም ገጽታ ግንባታ ድረስ እጅግ ከፍተኛ ፋይዳዎችን የሚያስገኘው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
