
በአማራ ክልል የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የሽልማት እና የዕውቅና መርሐ ግብር ተካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ጥራት ያለው ትምህርት ለክልሉ ሰላም፣ ልማት እና ብልጽግና መሠረታዊ መሣሪያ መኾኑን ገልጸዋል። የክልሉ መንግሥትም በትኩረት የሚመለከተው ዘርፍ መኾኑን ተናግረዋል።
ትምህርት የሕይወት ዘይቤ የሚቀረጽበት፣ የፍትሐዊ ሃብት ክፍፍል ማሥፈጸሚያ መሣሪያ፣ የኢኮኖሚ ማስተካከያ፣ የርትዕ ማኅበረሰብ የሚታነጽበት ሥርዓት መኾኑን በማመን መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራበት ነው ብለዋል። የትምህርት ጥራቱን ለማሻሻል የትምህርት ቤቶችን ገጽታ በማሻሻል እና በዘርፉ ያለውን ችግር ለመፍታት በቁርጠኝነት ይሠራል ነው ያሉት።
ከፍተኛ ውጤት ያመጡት ተማሪዎች ለዩኒቨርሲቲ መግቢያ ያስመዘገቡት ብቻ ሳይኾን በችግር ውስጥ የማለፍ፣ የጥንካሬ፣ የከፍታ እና የአሸናፊነት ምልክት የሚኾን ነው ብለዋል። የዓላማ ጽናት፣ የማያቋርጥ ትጋት እና ከችግር በላይ ኾኖ የማሸነፍ ማሳያ ስለመኾኑም ጠቁመዋል።
ተማሪዎች “ያመጣችሁት ውጤት ለቤተሰቦቻችሁ፣ ለመምህራኖቻችሁ፣ ለክልላችን እና ለሀገራችን ኩራት እና ክብር ነው”ብለዋል። በትምህርት ሥርዓት ውስጥ ከፍተኛ ውጤት ማምጣት የስኬት መጀመሪያው እንጂ መጨረሻው እንዳልኾነም ጠቁመዋል።
ዛሬ የተሸለሙበት ውጤት ነገ ወደ ከፍተኛ ዕውቀት፣ ሙያዊ ብቃት፣ ምርምር እና ፈጠራ የሚያሸጋግራቸው መሠረት መኾኑን አስገንዝበዋል። ለዚህም ተማሪዎች ሁሌም ራሳቸውን በሥነ ምግባር እና በግብረ ገብ በመቅረጽ ለቀጣይ ሕይወት በኀላፊነት እንዲያዘጋጁ አሳስበዋል።
ከውጤታማ ተማሪዎች ጀርባ የወላጆች፣ የመምህራን፣ እና የትምህርት ተቋማት ክትትል እና ድጋፍ አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመኾኑ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል። መምህራን የዕውቀት አስተማሪ ብቻ አይደሉም ነው ያሉት። ትውልድን የበለጠ በሥነ ምግባር በመቅረጽም ጥረታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_14_2019_ዓ_ም
✍️ ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ !
