
በአማራ ክልል የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የዕውቅና መርሐ ግብር ተካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ መልዕክት ያስተላለፉት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) ከፍተኛ ውጤት ያመጡት ተማሪዎች በርካታ ችግሮችን አሳልፈው ለስኬት መብቃታቸው የትጋት እና የስኬታማነት ማረጋገጫ መኾኑን ተናግረዋል።
ከፍተኛ ውጤት ያመጡት ተማሪዎች ስኬታቸው የትናንት ትጋታቸው ውጤት፤ የዛሬ ውጤታቸው ደግም ለነገው ተስፋ ነው ብለዋል።
“እናንተ የአማራ ክልል የተስፋ ብርሃን ናችሁ” ነው ያሉት። ዛሬ የደረሱበትን ስኬት ወደ ተግባራዊ ለውጥ በመቀየር ማኅበረሰቡን ለማገልገል አስበው ቀጣዩን የትምህርት ጊዜ ጠንክረው እንዲቀጥሉም አሳስበዋል።
ዛሬ ዓለም የምትፈልገው ችግሮችን የሚለዩ፣ መፍትሔ የሚያመነጩ፣ በሥነ ምግባር የሚመሩ ባለሙያዎችን ነው ብለዋል። ተማሪዎችም ይህንን ተገንዝበው የማኅበረሰቡን ችግር ለመፍታት አልመው በቀጣዩ የትምህርት ጊዜያቸው በትጋት እንዲዘልቁ አስገንዝበዋል።
“ሁሌም ተማሩ፤ ዕውቀታችሁን አሳድጉ፤ ለታናናሾቻችሁ መልካም ምሳሌ ሁኑ፤ ካለፋችሁበት የበለጠ ጠንካራ ሁኑ ብለዋል። የቤተሰቦቻቸውን መስዋትነት፣ የመምህራንን ጥረት እና የማኅበረሰባቸውን ተስፋ ሁሌም ማሰብ እንደሚጠበቅባቸውም መክረዋል። በቀጣይ የዩኒቨርሲቲ ቆይታቸውም ዘመኑ የሚጠይቀውን ክህሎት እና ቴክኖሎጂ እንዲይዙ ጠቁመዋል።
የዛሬው ስኬት ወደፊት ለሚጠብቃችሁ ጉዞ ኀላፊነት የሚሰጥ እና መነሳሳትን የሚፈጥር በመኾኑ በቀጣይ ራሳቸውን ለምርምር፣ ለተሻለ ሙያ፣ ለተከታታይ ሽልማት ማዘጋጀት እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ጥላሁን ወርቅነህ ትምህርት የልማት መሠረት፤ የለውጥ ሞተር ነው ብለዋል።
የደረጃ ልዩነት መኖሩ የግድ ቢኾንም በ2018 የትምህርት ዘመን የማለፊያ ውጤት ያመጡት ተማሪዎች ሁሉም የክልሉ ጀግኖች ናቸው ብለዋል። በክልሉ የትምህርት ጥራት እንዲሻሻል በቀጣይም ቢሮው ከአጋር እና ባለድርሻ አካላት ጋር ቅንጅቱን አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_14_2019_ዓ_ም
✍️ ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ !
