💻 ለልዩ ፍላጎት ተማሪዎች የሚውል ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ።

10

 

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ከክሊንተን ኸልዝ አክሰስ ኢኒሼቲቭ እና ፓርትነር ኢን ኢጁኬሽን ጋር በመተባበር 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ የልዩ ፍላጎት ተማሪዎች ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የሥርዓት ትምህርት ዝግጅት እና ትግበራ ዳይሬክር ተወካይ ጌታነህ መንግሥት ድጋፉ በክልሉ ለ12 ትምህርት ቤቶች የልዩ ፍላጎት ተማሪዎች ለመማር ማስተማር የሚያገለግሉ ቁሳቁሶች ናቸው ብለዋል። የተደረገው ድጋፍ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ለሚደረገው ጥረት ትልቅ ድርሻ አለው ብለዋል።

የክሊንተን ኸልዝ አክሰስ ኢኒሼቲቭ አጋዥ መርሐግብር አሥተባባሪ ሥንታየሁ አወቀ ድርጅቱ በትምህርት እና በጤናው ዘርፍ ድጋፍ እያደረገ መኾኑን ገልጸዋል። በተለይም ችግር ያለባቸውን ሕጻናት በመለየት ድጋፍ ማድረጋቸውን ነው ያስረዱት። ይህም ልጆት ተገቢ የኾነ ትምህርት ከእኩዮቻቸው ጋር እንዲያገኙ ያደርጋል ብለዋል።

ለልዩ ፍላጎት ተማሪዎች ከተደረጉ ድጋፎች መካከል ኮምፒውተር፣ ኘሮጀክተር፣ ስሌት፣ የብሬል መጻፊያ፣ የብሬል ወረቀት፣ ሞንቶሶሪ፣ ማጉያ መነጽር፣ የመራመጃ ዱላ እና ሌሎችም ይገኙበታል።

የአማራ ክልል አካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽን ኘሬዝዳንት ፍሬሰላም ዘገዬ እንዳሉት በክልሉ 98 በመቶ የሚኾኑ የልዩ ፍላጎት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ናቸው። የመጡትም ቢኾን በትምህርት ቁሳቁስ እጥረት ተገቢ ትምህት እያገኙ አይደለም ብለዋል።

የተደረገው ድጋፍ የልጆችን ችግር የሚፈታ እንደኾነም ጠቁመዋል። ለተደረገው ድጋፍም አመሥግነዋል። የልጆችን የነገ ተሥፋ ብርሃን ለማድረግ መንግሥት እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት እንደየ አካል ጉዳታቸው እየለዩ ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኅላፊ ሙሉዓለም አቤ (ዶ.ር) በከተማ አሥተዳደሩ በርካታ የልዩ ፍላጎት ተማሪዎች መኖራቸውን ገልጸዋል። ድርጅቱ በከተማ አሥተዳደሩ በትምህርት ዘርፉ እገዛ እያደረገ እና የልዩ ፍላጎት ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመጡ ሥራዎችን እየሠራም ነው ብለዋል።

#አሚኮ #አማራክልል #education #ኢትዮጵያ 🇪🇹
#ባሕር_ዳር #መስከረም_14_2019_ዓ_ም

ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለኝ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article‎ባሕር ዳር የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ እንግዶችን ለመቀበል ተዘጋጅታለች።
Next article“ከተለዋዋጭ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመሻገር አቅምን ማሠባሠብ ይገባል”