
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በልማት፣ በኢኮኖሚ እና በመሠረተ ልማት ዘርፎች መጠነ ሰፊ ውጤቶችን እያስመዘገበች ትገኛለች። ከእነዚህ መካከል በከተሞች እየለማ የሚገኘው እና የነዋሪዎቿን የአኗኗር ዘይቤ በመሠረታዊነት እየቀየረ ያለው የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት አንዱ ነው።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ሀሳብ አመንጭነት የተጀመረው ይህ ፕሮጀክት ረጅም ዘመናት የዘለቁ የከተሞች መጨናነቅን፤ የመሠረተ ልማት እጥረቶችን እና የአሥተዳደር ጉድለቶችን በመቅረፍ ከተሞችን ዘመናዊ፣ ጽዱ እና ለኑሮ ተስማሚ እያደረገ ይገኛል። አዲስ አበባን እንደ መነሻ ያደረገው ይህ ስኬታማ ተሞክሮ በአሁኑ ወቅት አሕጉራዊ ተምሳሌትነቱን እያረጋገጠ በሀገሪቱ የተለያዩ የክልል ከተሞች ተስፋፍቷል።
ቀደም ሲል ለዕግረኞች እና ለአካል ጉዳተኞች ፈታኝ የነበሩ መንገዶች ዛሬ ሰፊ እና ጥራት ባላቸው ንጣፎች፣ የእግረኛ መንገዶች እና የብስክሌት መስመሮች ተተክተዋል። የመዝናኛ ፓርኮች እና የማረፊያ ስፍራዎች መዘጋጀታቸው የዜጎችን ማኅበራዊ እና ሰብዓዊ ክብርም ከፍ አድርጎታል።
የዚህ ዓይነቱ ሰፊ የእግረኛ እና የብስክሌት መንገድ ዝርጋታ እንደ ኮሎምቢያዋ ቦጎታ ከተማ የመሠረተ ልማት እና የከተማ ማደስ ስትራቴጂ ጋር ይመሳሰላል። ቦጎታ መንገዶቿን ከተሽከርካሪ ይልቅ ለሰዎች ምቹ በማድረግ የዜጎችን አካላዊ ጤና እና ማኅበራዊ ትስስር ማሳደግ እንደቻለች ሁሉ የኢትዮጵያ የኮሪደር ልማትም የሰዎችን የነጻነት እና የደኅንነት ስሜት ማዕከል ያደረገ አሠራርን ተከትሏል።
በዘመናዊ የጎዳና መብራቶች እና በደኅንነት ካሜራዎች የታገዙት የኮሪደር ልማቶች ከተሞች በቀን ብቻ ሳይኾን በሌሊትም ንቁ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲኖራቸው አድርገዋል። ይህም የ24 ሰዓት የሥራ ባሕልን በመፍጠር ለአያሌ ወጣቶች እና ነጋዴዎች አዲስ የሥራ ዕድል ከፍቷል፤ ሀገሪቱንም ለቋሚ የኮንፈረንስ፣ የንግድ እና የባሕል ቱሪዝም ምቹ መዳረሻ እያደረጋት ይገኛል።
የኮሪደር ልማቱ መሠረተ ልማት ከመዘርጋት ባለፈ ከተሞችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ የማዘመን ሥራን አካቷል። ከቴክኖሎጂ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ዘመናዊ የትራፊክ ቁጥጥር ሥርዓቶች እና የስማርት ከተማ መተግበሪያዎች እየተዘረጉ ይገኛሉ። በተጨማሪም መጠነ ሰፊ የችግኝ ተከላ እና የወንዞች ዳርቻ ልማት ከተሞች ከአየር ንብረት ለውጥ እና ከሙቀት እንዲጠበቁ እያደረገ ነው።
በወንዞች ዳርቻ ልማት እና በአረንጓዴ ስፍራዎች ማስፋፋት ረገድ የደቡብ ኮሪያዋ ሴኦል ከተማ ያካሄደችው የ”ቼዮንግዬቾን” ወንዝ ማደስ ፕሮጀክት ተጠቃሽ ነው። ሴኦል የታፈነውን የከተማዋን ወንዝ ወደ አረንጓዴ ፓርክ በመቀየር የከተማዋን የሙቀት መጠን መቀነስ እና የቱሪስት መሳቢያ ማድረግ እንደቻለች ሁሉ በኢትዮጵያም የወንዞች ዳርቻ ልማት ተመሳሳይ ሥነ-ምህዳራዊ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
የኮሪደር ልማቱ በተለያዩ የዕድሜ እና የማኅበረሰብ ክፍሎች መካከል የዕለት ተዕለት መስተጋብር እንዲጠናከር በማድረግ የሕዝቦች አብሮነት እና ማኅበራዊ ትስስር እንዲጎለብት አድርጓል።
ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ በዲጂታል እና በአረንጓዴ ልማት የታገዘ ዘመናዊ የከተማ ሥርዓት ለመገንባት የምታደርገውን ጉዞ የሚያፋጥን ተምሳሌታዊ ተግባርም ነው።
በመረጃ ምንጭነት የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ድረ ገጽን ተጠቅመናል።
#አሚኮ #ኮሪደርልማት # #Ethiopia🇪🇹
#ባሕር _ዳር #መስከረም_13_2019_ዓ_ም
✍️ በምሥጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
