“የመገጭ ግድብ የሕይወታችን አለኝታ ሊኾን መጥቷል!” የአካባቢው አርሶ አደሮች

8

 

በጎንደር ዙሪያ ወረዳ የአዘዞ ጠዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አርሶ አደር አዳሙ ምትኬ እና አርሶ አደር ጀምበር ጠዴው፣ ክረምት በመጣ ቁጥር ቀልባቸው አያርፍም ነበር።

ለፍተው፣ ደክመው ያበቀሉት ሰብል እና ለም ማሳቸው በመገጭ ወንዝ የጎርፍ ማዕበል በየዓመቱ ሲወሰድባቸው ማየት የተደጋገመ ልብ ሰባሪ ትዕይንታቸው ነበር።

ለችግራቸው ዘላቂ መፍትሔ ይኾናል ተብሎ የተጀመረው የመገጭ ግድብ ፕሮጀክት ግንባታ ደግሞ ረጅም ጊዜ በመውሰዱ የመልማት አቅም ያለው መሬታቸው ላለፉት 18 ዓመታት ያለ አንዳች ጥቅም በከንቱ ቆይቷል።

ፕሮጀክቱ በታለመለት ጊዜ ባለመጠናቀቁም የአካባቢው ማኅበረሰብ በምሬት፣ ተስፋ በመቁረጥ እና በጥርጣሬ ዐይን ሲመለከተው መቆየቱን ነዋሪዎቹ አንስተዋል።

ኾኖም ግን ላለፉት ሁለት ዓመታት በተደረገ አርዓያነት ያለው ከፍተኛ ጥረት እና ቁርጠኝነት የግድቡ ግንባታ ተጠናቅቆ ለምረቃ በመብቃቱ ያ ሁሉ የዓመታት ስጋት እና ቁጭት ዛሬ በታላቅ ደስታ እና በተስፋ ብርሃን ተተክቷል ብለዋል።

የግድቡ መጠናቀቅ ለአካባቢው አርሶ አደሮች ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ፋይዳዎችን ይዞ መጥቷል፡

አርሶ አደሮች እንደሚሉት ከኾነ በየዓመቱ በመገጭ ወንዝ ሙሌት ይጠረግ የነበረው ለም ማሳ አሁን ላይ ከስጋት ነፃ ኾኖ መልሶ እንዲያገግም እና ለተሻለ ልማት እንዲውል አዲስ ዕድል ፈጥሯል።

በተለይም በዓመት እስከ ሦሥት ጊዜ በቋሚነት በመስኖ አልምተው ምርት እና ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ ታላቅ የበረከት በር ተከፍቶላቸዋል።

በአሁኑ ወቅት በመገጭ አቅራቢያ የሚገኘውን መሬታቸውን በተለያዩ አትክልት እና ፍራፍሬዎች እንዲሁም በስንዴ እና በቆሎ ሰብሎች ለማልማት በከፍተኛ ዝግጅት ላይ መኾናቸውንም አርሶአደሮቹ ገልጸዋል።

“ይህ ግድብ የሕይወታችን አለኝታ ሊኾን መጥቶል!” የሚሉት አርሶ አደሮቹ ይህ ለዘመናት ሲጠበቅ የነበረ ፕሮጀክት ለትውልድ የሚሻገር ዘላቂ አገልግሎት እንዲሰጥ በታላቅ ባለቤትነት ስሜት እንደሚጠብቁት እና እንደሚንከባከቡት አረጋግጠዋል።

#የመደመር_መንግሥት!#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_14_2019_ዓ_ም

✍️ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleአማራ ክልል አሕጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ኮንፈረንሶችን የማስተናገድ ብቃት ገንብቷል።
Next articleፈተናን ወደ ዕድል፤ የመገጭ ግድብ የስኬት ጉዞ 🇪🇹