ከጎርጎራ እስከ ወንጪ፤ የገበታ ለትውልድ እና የዘመናዊ ኢኮ ሪዞርቶች ስኬት

16
⛰️💵
ኢትዮጵያ “የሥልጣኔ እምብርት” እና “የመጀመሪያ የሰው ልጅ መገኛ” በመኾን የምትታወቅ እጅግ የበለጸገ የተፈጥሮ ሀብት ያላት ሀገር ናት። ከቅርብ ዓመታት ጀምሮ የሀገሪቱ የቱሪዝም ዘርፍ ወደ ዘመናዊ የለውጥ ጉዞ እየተሸጋገረም ይገኛል።
ሀብቶቹን በማስተዋወቅ እና ዘላቂነታቸውን በማስጠበቅ ለትውልድ ለማውረስ እየተሠራ ነው። እንደ ላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናት እና የጎንደር አብያተ መንግሥታት ባሉ ታሪካዊ ቅርሶች ላይ የተደረጉ የጥገና ሥራዎች ለዚህ ማሳያዎች ናቸው።
አዲስ አበባን ጨምሮ በሌሎች ከተሞች እየተከናወኑ ያሉት የኮሪደር ልማት ሥራዎች ከተሞቹን ውብ እና ለቱሪስቶች ምቹ በማድረግ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።
በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የኢኮ ሪዞርት መሥፋፋት እና የዘላቂነት ጉዞም ተጀምሯል። ገበታ ለትውልድ እና ገበታ ለሀገር ኘሮጀክቶች ትኩረት የተሠጣቸው ተግባራት ናቸው። እንደ ጎርጎራ፣ ወንጪ፣ ሃላላ ኬላ እና ሌሎችም ዘላቂ ቱሪዝምን የሚያስተዋውቁ፤ ተፈጥሮን ጠባቂ ዘመናዊ ኢኮ ሪዞርቶች እና ሎጂዎች መገንባታቸው የዘርፉን ሁለገብ ጉዞ በግልጽ የሚያሳዩ ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ቱሪዝም ከግብርናው፣ ከኢንዱስትሪው እና ከሌሎችም የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እያነቃቁ ከሚገኙ ዋና ዋና የእድገት ሞተሮች ውስጥ አንዱ መኾኑን መግለጻቸው ይታወሳል። በዘርፉ በተከናወኑ የኢኮኖሚ ሪፎርሞች እና የሀብት ማስተዋወቅ ሥራዎች አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከልነቷ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን የማስተናገድ አቅሟ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል ነው ያሉት።
🌍✨ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሞተር የኾነው የቱሪዝም ዘርፍ በቁጥር፣ በገንዘብ እና በሰዎች ፍሰት እጅግ እያደገ ይገኛል ብለዋል። ልክ እንደ ግብርናው፣ ኢንዱስትሪው፣ ቴክኖሎጂው እና ማዕድኑ ሁሉ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ መኾኑንም አንስተዋል።
በቀጣይም ችግሮችን በመለየት ይበልጥ በመሥራት፣ በማስተዋወቅ እና በማቀናጀት ስኬቶችን ማስመዝገብ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“ከሱማሊያ እስከ ምጽዋ ጫፍ የቀጣናው የሰላም ጋሻ”👏
Next articleመጭው ዘመንን ታሳቢ ያደረገው የኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ጉዞ