መጭው ዘመንን ታሳቢ ያደረገው የኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ጉዞ

18
🇪🇹
ኢትዮጵያ እንደ ሀገር መዋቅራዊ ለውጦችን እያመጣች ከምትገኝባቸው ዘርፎች መካከል ሀገሪቱን ወደ ዲጂታል ሥነ ምኅዳር የማሸጋገር ጉዞ አንዱ ነው።
ለዚህም የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ተቀርጾ በስኬት ተከናውኗል። በቁልፍ ዘርፎች ላይ በማተኮርም ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል።
በዚህ ስትራቴጂ ውስጥ የኢትዮ ኮደርስ መርሐ ግብርን ለክህሎት ማሳደጊያ፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ እና ለሰው ኀይል ግንባታ ወሳኝ ስትራቴጅ ተደርጎ ተሠርቶበታል።
የሳይንስ ሙዚዬም በዘመናዊ መንገድ ተደራጅቶ፣ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የሚታዩበት በወጣቶች እና ታዳጊዎች አዕምሮ ውስጥ የቴክኖሎጂ ፍቅርን የሚያሰርጽ ስትራቴጂካዊ ማዕከል ኾኗል።
የመጭው ዘመንን የቴክኖሎጂ ውድድር ታሳቢ በማድረግ በአፍሪካ የመጀመሪያ የኾነውን የኤ አይ ዩኒቨርሲቲ በመገንባት ላይ ይገኛል።
ለዜጎች አገልግሎትን የሚያሳልጥ፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ፣ ቀልጣፋ፣ ተደራሽ አሠራር ለመዘርጋት የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት በሥፋት ተግባራዊ እየተደረገም ይገኛል።
እነዚህ እና ሌሎችም የዲጂታል ዘርፎች ኢትዮጵያን በአፍሪካ የቴክኖሎጂ ማዕከል የመኾን ርዕይዋን በተጨባጭ ለማረጋገጥ እንደሚያስችሏትም ተስፋ ተጥሎባቸዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እንደተናገሩት በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ በተከናወኑ ተግባራት ዜጎች ቀልጣፋ፣ ወጭ ቆጣቢ እና ተደራሽ አገልግሎት እንዲያገኙ መሠረት ጥሏል።
በቴሌብር፣ በዘመን ገበያ እና በሞባይል ባንኪንግ አገልግሎት የሀገሪቱን የገንዘብ ዝውውር እና የክፍያ ሥርዓትን የቀየረ መኾኑን አንስተዋል።
የዲጂታል ሥነ ምኅዳር ለመገንባት ቁልፍ የኾነው ዲጂታል ፋይዳ የመታወቂያ ሥርዓት ለምቶ በስፋት ሥራ ላይ መዋሉንም አብራርተዋል። ለባንክ አገልግሎት፣ ለቀረጥ ሥርዓት እና ለተለያዩ የመንግሥት አገልግሎቶች ዋነኛ ማሳለጫ ኾኖ በማገልገል ላይ እንደሚገኝም አመላክተዋል።
📌ፈጠራን፣ ፍጥነትን እና እምርታን መሠረት ያደረገው ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 በስኬት ተጠናቅቆ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጅም እየተተገበረ ቀጥሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ.ር) ዲጂታል 2025 ስትራቴጂ መቶ በመቶ የተሳካ ነበር ብለዋል። የአገልግሎት ሰጭ ተቋማትም አገልግሎታቸውን በቴክኖሎጂ በማዘመን ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
በዲጂታል ፋይናንስ ዘርፍም በቴሌ ብር እና በሞባይል ባንኪንግ ስርዓቶች በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ዝውውር መፈጸሙን ተናግረዋል። ይህም ጊዜን ቆጥቧል፣ፍጥነት ጨምሯል ብለዋል።
የዲጂታል 2025 ስትራቴጂን እንደ መስፈንጠሪያ በመጠቀም ዲጂታል 2030 ስትራቴጂ ለዜጎች የአገልግሎት ተደራሽነትን ማረጋገጥ፣ ዕኩል የተጠቃሚነት ዕድል መፍጠርን እንዲኹም በዜጎች እና በተቋም መካከል እምነት መፍጠርን መሠረት ያደረገ መኾኑን አመላክተዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleከጎርጎራ እስከ ወንጪ፤ የገበታ ለትውልድ እና የዘመናዊ ኢኮ ሪዞርቶች ስኬት
Next articleበጀግንነት እሴት የደመቀች ሀገር – ኢትዮጵያ