
የአፍሪካ ቀንድ እና የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና በርካታ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ጂኦ-ፖለቲካዊ ውጥረቶች የሚስተዋሉበት፤ እጅግ ተለዋዋጭ ሁነቶች የሚስተናገዱበት፣ አያሌ ፍላጎቶች የሚንጸባረቁበት፣ የስበት ማዕከል እና የተጽዕኖ ቀጣና ነው።
የ4ኛ ትውልድ ቴክኖሎጂ የታጠቀው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ለምሥራቅ አፍሪካ ያለው ጠቀሜታ ምንድን ነው?👇
ያልተረጋጋ እና በርካታ ግጭቶች በሚስተዋሉበት በዚህ ቀጣና ውስጥ ኢትዮጵያ ለቀጣናው የሰላም እና የደኅንነት ዋና አምድ በመኾን ዘላቂ ሚናዋን አስጠብቃ ዘልቃለች። ለዚህም ከጥንት ጀምሮ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት አጽንታ የቆየች፣ ጠንካራ የጸጥታ እና የደኅንነት ተቋማት የገነባች ሀገር መኾኗ በምክንያትነት ይገለጻል።
በተለይም በቅርብ ዓመታት ሀገሪቱ የመከላከያ ኀይሏን በሰው ኀይል፣ በሥልጠና እና በቴክኖሎጂ መገንባቷ በቀጣናው ያላትን ተሰሚነት እንድታስቀጥል አስችሏታል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጥንካሬ በቁጥር ብዛት ብቻ የሚገለጽ አይደለም። ይልቁንስ ለሀገሩ ባለው እምነት፣ ጽናት፣ ቁርጠኝነት፣ በታጠቀው ቴክኖሎጂ፣ በገነባው አቅም እና በውጊያ ጥበቡ የሚለካ ነው።
ኢትዮጵያ ወታደራዊ አቅሟን ለሰላም፣ ለቀጣናዊ ትብብር እና ለሕዝቦች አብሮነት ዋስትና አድርጋ በማጠናከሯ በቀጣናው ያለውን የኀይል ሚዛን ለማስጠበቅ ዕድል ፈጥሮላታል። ይህ የሠራዊቷ ጥንካሬ የሀገሪቱን ድንበር ከመጠበቅ አልፎ፣ የምሥራቅ አፍሪካ አስተማማኝ የሰላም ዘብ ኾኗል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እንደተናገሩት የኢትዮጵያ ወታደራዊ ዝግጅት በድፍን አፍሪካ ሰላምን ለማረጋገጥ፣ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ላሉ ሀገራት ደግሞ አለኝታ፣ መከታ እና ጋሻ ለመኾን ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ወታደራዊ አቅም ማደግ ለጎረቤት ሀገራት ስጋት ሳይኾን ለቀጣናው ሰላም ዋስትና የሚሰጥ መኾኑን ተናግረዋል። ጎረቤቶቻችን ሰላም ሲኾኑ እኛም ሰላም እንደምንኾን፣ ሲረጋጉ እኛም እንደምንረጋጋ አስበን እንሠራለን ነው ያሉት።
ይህንን ታሳቢ በማድረግ በተለይም ባለፉት አምስት ዓመታት በሰው ኀይል፣ በቴክኖሎጂ እና በምድር ኀይል የኢትዮጵያን አቅም ከፍ የሚያደርጉ ሥራዎች መሠራታቸውን ተናግረዋል። በአየር ኀይል በኩልም የ4ኛውን ትውልድ የመዋጋት ብቃት ተጎናጽፏል። በምድር የነበረውን ሥልጠና ወደ ባሕር በማስፋት ዘመኑን የዋጀ የውጊያ ቴክኖሎጂ ታጥቋል ነው ያሉት።
“ወንድም ሕዝቦችን ደግፈን በቀጣናው ከሱማሊያ ጫፍ እስከ ምጽዋ ጫፍ በባሕር የሚያጋጥሙ ሽብሮችን ጭምር ለመከላከል እና ልማትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ኀይል ገንብተናል” ብለዋል።
ኢትዮጵያ የሠለጠነ፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን የታጠቀ፣ ውጊያን በአጭር ጊዜ የሚጨርስ፣ ለድፍን የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ጋሻ የኾነ ኀይል ገንብታለች ነው ያሉት። ይህም በቀጣናው ሽብር እንዳይፈጠር፣ ሲፈጠርም በአጭር ጊዜ ለመቋጨት ዓላማ ያደረገ መኾኑን ጠቁመዋል።
የዚምባቡዌ ሠራዊትን ያሠለጠነ፤ ለኮሪያ፣ ለሩዋንዳ፣ ለቡሩንዲ፣ ለሶማሊያ፣ ለሱዳን፣ ለደቡብ ሱዳን፣ ለላይቤሪያ እና ለብዙ ሀገራት ሰላም መስዋትነትን የከፈለ ተቋም ነው ብለዋል። ለዚህም የዓለም አቀፍ ዕውቅና ተችሮታል።
ከአሁን በፊት ከኢትዮጵያ ውጭ የተካሄዱትን የዓለም አቀፍ ስምሪቶች በብቃት ሲፈጽም እንደኖረ ሁሉ በዚህ ዘመንም ያንን ታሪክ የሚደግም ለሀገሩ ክብር የሚሰዋ ኀይል መገንባቱንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።
#አሚኮ #Ethiopia🇪🇹 #Africa
#ባሕር_ዳር #መስከረም_12_2019_ዓ_ም
በአሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
