💥 ማስቆም የማይቻለው አዲሱ የኢትዮጵያ ትግል

45

 

ኢትዮጵያ ከድኅነት እና ኋላቀርነት ለመላቀቅ በትጋት እየሠራች ነው። ከዘመኑ ጋር እኩል ለመጓዝም ለዲጂታል ዘርፍ እና ለታላላቅ ሜጋ ፕሮጀክቶች ልዩ ትኩረትን ሰጥታለች። ፈተናዎችን ወደ ዕድል እየቀየረች ታላላቅ መሠረተ ልማቶችን ገንብታ አስመርቃለች፤ እየገነባችም ትገኛለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ምርቃት ወቅት ባደረጉት ንግግር ሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይኾን ለጥቁር ሕዝቦች ታሪክ ኾኖ የሚኖር ታላቅ ገድል ነው ብለዋል። ጥቁሮች እንደምንችል እና እንደምናሳካ አሳይተናልም ነው ያሉት።

ገደሉን ተሻግረናል፤ ገድልን በሕዳሴ አትመናል ብለዋል። በቀጣይ የኢትዮጵያ ብልጽግናን የሚያረጋግጡ፤ የአፍሪካን ልጆች ቀና የሚያደርጉ ሜጋ ፕሮጀክቶች ዕውን ይኾናሉ ነው ያሉት። ኢትዮጵያ ተረጅነቷ አብቅቶ ረጅ እንደምትኾንም ተናግረዋል።

👉ኢትዮጵያን ከተረጅነት ወደ ረጅነት የሚያሻግሩ ሜጋ ፕሮጀክቶች።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በጉባ ብሥራቶች ከ30 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሃብት የሚፈስባቸው ሜጋ ፕሮጀክቶችን እንደምትገነባ ተናግረዋል።

✅ለሰላማዊ ዓላማ የሚውል የኒውክሌር ማብለያ፤

✅በአፍሪካ ግዙፍ የኾነ የአውሮፕላን ማረፊያ፤

✅የጋዝ ፋብሪካ፤

✅የማዳበሪያ ፋብሪካ

✅የ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቤቶች ግንባታ ሜጋ ፕሮጀክቶች በሀገሪቱ እንደሚገነቡ ጠቅሰዋል።

👉 ሜጋ ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ መግባት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የመጀመሪያውን የተፈጥሮ የጋዝ ፕሮጀክት ባስመረቁበት ወቅት ኢትዮጵያውያን በትጋት በመሥራት እናንሠራራለን፤ በውጤቱም እናበራለን ብለዋል። የኢትዮጵያን ልማት እናረጋግጣለን ነው ያሉት።

የጋዝ ፕሮጀክቱ 1ሺህ ሜጋ ዋት ኀይል በማመንጨት ለኢትዮጵያ ብርሃን ይኾናል ብለዋል። የጋዝ ፕሮጀክቱ ለማዳበሪያ ማምረቻ ዋነኛ ግብዓት ኾኖ እንደሚያገለግልም በወቅቱ ተናግረዋል። የኢትዮጵያን ልማት ማንም ሊያስቆመው እንደማይችልም ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁለተኛውን የጋዝ ፕሮጀክት ባስጀመሩበት ወቅት ደግሞ ዜጎችን ከድኅነት አረንቋ ለማውጣት በትጋት መሥራት ያስፈልጋልም ነው ያሉት።

በሚቀጥሉት 6 ዓመታት ትላልቅ ሜጋ ፕሮጀክቶች ተሠርተው እንደሚመረቁም ነው ያነሱት። ዓይንን በመግለጥ እና በትብብር የኢትዮጵያን ዕድገት ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

የአፍሪካ ግዙፉን የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ የጀመረችው ኢትዮጵያ የዕድገት ሥብራት የኾነውን የሎጂስቲክ ችግር ለመፍታት ትልቅ መሠረት ይኾናታል። የኢትዮጵያ ተፈጥሮ መለመን ሳይኾን መርዳት፤ ለአፍሪካ ኩራት መኾን እንደኾነም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የትግል ስልት ተቀይሯል፤ የእኛ የትግል ስልት ዛሬ ሠርተን ነገን መዋጀት፤ ለነገ ትውልድ የሠመረ ማድረግ ነው ብለዋል። ሜጋ ፕሮጀክቶቹ ሲጠናቀቁ በአፍሪካ ቀዳሚውን ኢኮኖሚ ኢትዮጵያ ትገነባለች ነው ያሉት። አሁን በጉባ የተበሠሩት ብሥራቶች ተግባራዊ እየተደረጉ ነው።

#አሚኮ #ሜጋ_ፕሮጀክት #ኢትዮጵያ🇪🇹

#ባሕር_ዳር #መስከረም_11_2019_ዓ_ም

ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleፈተና የሚያበረታት፣ ማዕበል የማያናውጣት።🇪🇹
Next articleከ28 በላይ የሚኾኑ የሰብል በሽታዎችን መለየት የሚያስችል ኤ አይ (AI) ያበለጸገው ወጣት !