
የውስጥ እና የውጭ ጠላቶች ኢትዮጵያውያንን በሐሰት ፕሮፓጋንዳ በመከፋፈል ሀገሪቱን ለማፍረስ ከትናንት እስከ ዛሬ ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም፤ ወደፊትም አይሳካላቸውም ሲሉ የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት ገልጸዋል።
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አክለውም እንደ ትናንቱ ሁሉ ዛሬም የውስጥ እና የውጭ ባንዳዎች እንዲሁም ታሪካዊ ጠላቶቻችን ኢትዮጵያን በቀጣናው ደካማ ሀገር ለማድረግ የጥፋት ጥምረት ፈጥረው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ ብለዋል።
ኾኖም ግን በጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና በሀገር ወዳዱ ሕዝብ የተቀናጀ ትግል ሴራቸው እና ጥረታቸው እየከሸፈ ይገኛል ሲሉም ተናግረዋል።
“የውስጥ እና የውጭ የጥፋት ኀይሎችን በጋራ በመታገል፣ የባሕር በር ጥያቄን ለማስመለስ በጋራ የምንቆምበት ጊዜ አሁን ነው” ብለዋል።
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ዛሬ ሕዝቡ ወደ አደባባይ በነቂስ በመውጣት ያሳየው አጋርነት፣ ሠራዊቱ ሕዝባዊ ደጀን ያለው ግዙፍ ሀገራዊ
አለኝታ መኾኑን እና ሕዝቡም በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የማይደራደር መኾኑን በተግባር ያረጋገጠበት ነው ብለዋል። ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ከውስጥ እና ከውጭ የኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር ጥምረት ለፈጠሩ እና በጫካ ለሚገኙ የታጠቁ ኀይሎች የሰላም ጥሪም አቅርበዋል።
በጥፋት እና በውድመት የሚመለስ ጥያቄም ኾነ የሚሳካ ዓላማ እንደሌለ በመጠቆም የታጠቁ ኀይሎች የሰላም አማራጭን በመጠቀም ከታሪክ ተወቃሽነት ነፃ እንዲኾኑ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በከተማ አሥተዳደሩ ለመከላከያ ሠራዊቱ እና ለሌሎች የጸጥታ ኀይሎች በተደረገው የድጋፍ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አርሶ አደሮች፣ ፈረሰኞች እና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በነቂስ ተሳታፊ ኾነዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
