
ወጣት አብርሐም አስራት የወልድያ ከተማ ነዋሪ ነው። ወጣቱ ከጓደኞቹ ጋር በመኾን በተለያዩ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤ አይ) እና ሮቦቲክስ መፍትሔዎችን በማበልጸግ ላይ ተሠማርቷል።
አሚኮ ከአልማ ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የብቁ ወጣቶች የሥራ ፈጠራ ውድድር ላይ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውጤቶቹንም አቅርቧል። ወጣት አብርሐም አስራት በዚህ ወቅት እንዳስረዳው የተለያዩ የኤ አይ ቴክኖሎጂዎችን እያበለጸገ ይገኛል።
ሰዎች ለመናገር የሚቸግራቸውን በሽታዎች በመለየት መናገር፣ አርሶ አደሮች የሚያመርቱት ሰብል በበሽታ ሲጠቃ የበሽታውን አይነት እና የሚያስፈልገውን መድኃኒት መጠቆም የሚችል ኤ አይ ማበልጸግ እንደቻለ አስረድቷል።
ካበለጸጋቸው የሰው ሠራሽ አስተውሎት የቴክኖሎጂ ውጤቶች መካከል የግብርና ሥራን የሚያሳልጥ የኤ አይ ፈጠራ ይገኝበታል።
አብርሐም እንደገለጸው ያበለጸገው የሰው ሠራሽ አስተውሎት በአንድ ካሜራ ከ28 በላይ የሰብል በሽታዎችን መለየት ይችላል። በተጨማሪም ከ5 በላይ የእንስሳት በሽታዎችንም የመለየት አቅም አለው ብሏል።🤖🌱
ወጣት አብርሐም እስከ አሁን አበልጽጎ ወደ ሥራ ያስገባውን የኤ አይ መፍትሔዎች አርሶ አደሮችን እና ተማሪዎችን አሠልጥኖ እንዲጠቀሙበት ማድረጉንም አብራርቷል። 📷
ቴክኖሎጂው የምልክት ቋንቋንም መረዳት እና መተርጎም ይችላል ነው ያለው። የሕግ ጉዳዮችን እስከ ማማከር የሚደርስ የኤ አይ መፍትሔዎችንም በማበልጸግ ላይ እንደሚገኝ አስረድቷል።
የቴክኖሎጂ ሥራውን ከኢንሳ ጋር በመተባበር እየሠራ እንደሚገኝም አብራርቷል። በቀጣይም በዓለም ዓቀፍ የቴክኖሎጂ እና ሮቦቲክስ አውደ ርዕይ ላይ ሀገሩን ወክሎ ለመሳተፍ ዕድል እንዳገኘ ገልጿል።🔐
🎯 ወጣቱ በቀጣይ ለእያንዳንዱ ችግር መፍትሔዎችን የሚያመላክት የሰው ሠራሽ አስተውሎት እና የሮቦቲክስ የፈጠራ ውጤቶችን በማበልጸግ ወደ ገበያ እንደሚያቀርብ ነው የተናገረው።
#አሚኮ #Innovation #Ethiopia🇪🇹
#ባሕር_ዳር #መስከረም_12_2019_ዓ_ም
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
