ፈተና የሚያበረታት፣ ማዕበል የማያናውጣት።🇪🇹

25

 

ታሪክ እንደሚያስረዳው ኢትዮጵያ ከጥንታዊ የሥልጣኔ ዘመን እስከ አሁን ድረስ በዓለም መድረክ የራሷ የኾነ ደማቅ ታሪክ ያላት ሀገር ናት። በዚህ የረጅሙ ታሪኳ ውስጥ አያሌ ውስጣዊ እና ውጫዊ ፈተናዎች ገጥሟታል።

በተለያዩ ዘመናት ከውጭ ወራሪዎች ከተጋረጡባት የሉዓላዊነት ስጋቶች እስከ ውስጣዊ የሥልጣን እና የፖለቲካ ሽኩቻዎች ድረስ በርካታ “የእሳት ላይ እርምጃዎችን” በጽናት እያለፈች ተጉዛለች።

በዚህ ጉዞዋ ሁሉ በወርቅ ቀለም የተጻፈ የሉዓላዊነት አርማን አትማ፣ በዓለም ሀገራት የገዘፈ ማንነቷን ገንብታ፣ ዳር ድንበሯን ጠብቃ፣ አንድነቷን አጽንታ ዘልቃለች። የውጭ ተጽዕኖን በሕዝቧቿ አንድነት እየመከተች፤ ውስጣዊ አለመግባባቶችን በጋራ ማንነት እያሸነፈች ብሔራዊ ክብሯን አጽንታለች።

በየዘመናት የሚነሱባት የፖለቲካ ማዕበሎች ሳያናውጣት ለዛሬው ትውልድ ደርሳለች። የሚፈራረቁባት ፈተናዎች ሕዝቦቿን ለበለጠ ሀገራዊ ጥቅም እና ለሉዓላዊነት ክብር በአብሮነት እንዲቆሙ አድርጓቸዋል።​🔥

​የታሪክ መጻሕፍት እና የታሪክ ተመራማሪዎች እንደሚያስረዱት የኢትዮጵያ ታሪክ የታላቅነት፣ የድል እና የፈተና ጥምረት ነው። ከዘመነ መሳፍንት እስከ የሰሜኑ ጦርነት ድረስ በተለያዩ ዘመናት የገጠሟትን የውስጥ ግጭቶች በጽናት አልፋለች። ከግብጽ ወረራ እስከ ጣልያን የቅኝ ግዛት ጦርነት ድረስ ያጋጠሟትን የውጭ ተጽዕኖዎች በአንጸባራቂ ገድል፣ በሉዓላዊነት ጋሻ ድል አድርጋለች።

​ዛሬም ቢኾን የሀገሪቱን ዕድገት እና ጥንካሬ የማይሹ ኀይሎች ኢትዮጵያን ለማፍረስ እና ለመከፋፈል ቢጥሩም ሀገሪቱ የማትወድቅ መኾኗን ደጋግማ አሳይታለች። በእነዚህ የታሪክ አጋጣሚዎች ሁሉ ሕዝቦቿ በጋራ በመቆም ሉዓላዊነታቸውን ያስከበሩበት መንገድ ልዩ መግለጫዋ ኾኗል።

የኢትዮጵያ ጥንካሬ የሚመነጨው ከሕዝቦቿ ጥልቅ ብሔራዊ ማንነት፣ ከጀግንነት እና ከታሪካዊ መሠረት ነው። የቱንም ያክል የሀሳብ እና የፍላጎት ልዩነት ቢኖራቸውም ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ጉዳይ ግን ልዩነት እንደሌላቸው የሚያስረዳ ነው።

ኢትዮጵያ በታሪኳ በገጠሟት በርካታ ማዕበሎች እና ፈተናዎች ሳትናወጥ ዘልቃለች። ዛሬም አዳዲስ ፈተናዎች ቢጋረጡባትም የፈተናዎች ብዛት ይበልጥ የሚያጠነክሯት ሀገር ኾናለች። የውስጣዊ አንድነቷን አጽንታ የነፃነት ምልክት፣ የፓን-አፍሪካኒዝም እና የአህጉራዊ ተስፋ ምልክት ኾና የቆየችበትን የታሪክ አሰላለፍ ዛሬም ድረስ አስቀጥላዋለች።

ኢትዮጵያውያን አባቶች በአንድ ድምጽ “ዳሯን እሳት መሐሏን ገነት ያድርግልን” እያሉ የሚጸልዩላት፣ ሰንደቋ በእሳት በተፈተኑ መሪዎቿ፣ በማይወላውሉት ዜጎቿ በዓለም አደባባይ ከፍ ብሎ መውለብለቡን ቀጥሏል።🌍

የሕዝቦቿ የጋራ ጽናት፣ የሀገራዊ ጥቅም ማስከበር ቁርጠኝነት እና ጥልቅ ታሪካዊ መሠረት ኢትዮጵያ ፈጽሞ የማትወድቅ፣ እንዲያውም በፈተናዎች ውስጥ አልፋ ሌሎችን የምታነሳ ሀገር ኾና እንድትቀጥል አድርጓታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እንደገለጹት የኢትዮጵያን ዕድገት የማይሹ አካላት በተለያዩ ዘመናት “አለቀላት፣ ልትወድቅ ነው፣ ልትፈርስ ነው ይላሉ፤ ኢትዮጵያ ግን አትወድቅም ብቻ ሳይኾን የወደቁትን ታነሳለች። ከራሷም አልፋ የተኙትን እያነሳች፣ መልማት እና መበልጸግ የሚገባቸውን አንቅታ ወደ ብልጽግና ጎዳና ትወስዳለች ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

የቀደሙት አባቶች እና እናቶች ደማቸውን አፍስሰው፣ አጥንታቸውን ከስክሰው ለዛሬው ትውልድ አስረክበዋል። የዛሬው ትውልድም የአባቶችን አደራ ጠብቆ፣ የወደፊቷን ኢትዮጵያ በጠንካራ መሠረት ላይ የመገንባት ታሪካዊ ኀላፊነት አለበት።💪

#አሚኮ #ተፈትና_እንደወርቅ_የጸናች_ሀገር #ኢትዮጵያ🇪🇹

#ባሕር_ዳር #መስከረም_11_2019_ዓ_ም

ዘጋቢ፦ አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleኢትዮጵያ የአፍሪካ ምልክት እና አርዓያ ኾና ዘልቃለች።🇪🇹
Next article💥 ማስቆም የማይቻለው አዲሱ የኢትዮጵያ ትግል