
ኢትዮጵያ “የአፍሪካ ችግሮች ለአፍሪካውያን መፍትሔ” የሚለውን መርህ በመከተል የአህጉሪቱን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ፈተናዎች በራስ አቅም እና ሉዓላዊነት የመፍታት ታሪካዊ እና ዘላቂ ሚናዋን አጠናክራ ቀጥላለች።
በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር አበራ ታደሰ እንደገለጹት የኢትዮጵያ ታሪክ ከአፍሪካ ወንድማማችነት እና ከፓን-አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ጋር በጥልቅ የተቆራኘ ነው።
መምህር አበራ እንደሚሉት በ1888 ዓ.ም የተገኘው የታላቁ የዓድዋ ድል መላው ጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ተምሳሌት እንዲኾኑ እና አፍሪካውያን የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው መወሰን እንደሚችሉ ያስመሰከረ ታሪካዊ ማኅተም ነው።
አፍሪካ በቅኝ ግዛት ቀንበር ስትማቅቅም ኢትዮጵያ ነጻነቷን አጽንታ በመቆየት ለነጻነት ትግሉ መነሻ እና የድጋፍ ማዕከል ኾና አገልግላለች።
በተጨማሪም አዲስ አበባ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአሁኑ አፍሪካ ኅብረት) ምሥረታ እምብርት ኾና ማገልገሏን እና የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጥረት ለአህጉሪቱ አንድነት የጎላ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቁመዋል።
በሀገር ውስጥ የተለያዩ መንግሥታት ቢፈራረቁም ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አንድነት ያላትን ጽኑ አቋም ሳታወላውል ማስቀጠሏን ያመለከቱት መምህሩ ከንጉሡ ዘመን ጀምሮ በኮንጎ፣ በሱዳን እና በሶማሊያ የሰላም አስከባሪ ኀይል በመላክ ትልቅ ድርሻ ተወጥታለች ብለዋል።
በቅርቡም የሰሜኑ ጦርነት በአፍሪካ ኅብረት አሸማጋይነት በፕሪቶሪያ ስምምነት ሰላማዊ ፍጻሜ ማግኘቱ ሀገሪቱ ለአፍሪካዊ መፍትሔ ያላትን ጽኑ ዕምነት የሚያሳይ ማረጋገጫ መኾኑን ገልጸዋል።
ከፖለቲካው ባሻገር በኢኮኖሚ እና በመሠረተ ልማት ዘርፍ ኢትዮጵያ የምታደርገው አስተዋጽኦ የጎላ መኾኑ ተመላክቷል። የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ኀይል ለጎረቤት ሀገራት ማዳረስ፣ የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ ንግድ ቀጣና ስምምነትን መተግበር እና በዓለም አቀፍ አየር መንገድ አማካኝነት አህጉሪቱን ከዓለም ጋር ማስተሳሰር ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
የአፍሪካ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ የሚያገኙት ከውጭ ከሚመጡ ጣልቃ ገብነቶች ይልቅ አፍሪካውያን እርስ በእርስ በመነጋገር እና የጋራ ተጠቃሚነትን በማስቀደም በባለቤትነት መንፈስ ሲንቀሳቀሱ ብቻ መኾኑንም አመላክተዋል።
#አሚኮ #ለአፍሪካ ችግሮች #የጋራመፍትሔ #ኢትዮጵያዊ 🇪🇹
#ባሕር_ዳር #መስከረም_11_2019_ዓ_ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
