የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የትግራይ ቴሌቪዥንን አገደ።

70

 

የትግራይ ቴሌቪዥን መታገዱን አስመልክቶ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን መግለጫ ሰጥቷል።

በመግለጫውም በኢፌዴሪ መንግሥት እና በሕወሃት መካከል በፕሬቶሪያ የተፈጸመውን የሰላም ስምምነት ተከተሎ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አሥተዳደር ጋር ባደረገው ውይይት እና በተደረሰበት ስምምነት መሠረት ቀደም ሲል በትግራይ ቴሌቪዥን ላይ ተጥሎ የነበረው እገዳ ተነስቶ ወደ ሥራ መመለሱን አስታውሷል።

ከዚህም በተጨማሪ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ለትግራይ ቴሌቪዥን ጋዜጠኞች እና ባለሙያዎች የሰላም ግንባታ እና የሙያ ብቃት ማሳደጊያ ሥልጠናዎችን በመስጠት ሚዲያው ወደ ሕገ መንግሥታዊ እና ሙያዊ መስመር እንዲመለስ ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።

ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የትግራይ ቴሌቪዥን በተሰጠው ዕድል ተጠቅሞ እና የሙያ ሥነ ምግባር አክብሮ አገልግሎት መስጠት ሲገባው፤ የሀገርን እና የሕዝብን ደኅንነት፣ ብሔራዊ ጥቅምን አደጋ ላይ የሚጥሉ፤ ወደ ግጭት የሚገፋፉ እና ጽንፈኝነት የሚያበረታቱ መልዕክቶች በተከታታይ እየተላለፉበት እንደሚገኝ የሚዲያ ይዘት ክትትል ግምገማችን ውጤት ያረጋግጣል ብሏል መግለጫው፡፡

በመኾኑም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በሕግ የተጣለበትን ኀላፊነት መሠረት በማድረግ ከዛሬ ጀምሮ በትግራይ ቴሌቪዥን ላይ ላልተወሰነ ጊዜ እገዳ መጣሉን ገልጿል።

✍️ ማሳሰቢያ፦

ማንኛውም ዲጂታል፣ የብሮድካስትም ኾነ የሕትመት ሚዲያ የትግራይ ቴሌቪዥንን እንደ መረጃ ምንጭ መጠቀም ወይም የቴሌቪዥን ጣቢያው በሕገ ወጥ መንገድ የሚያሠራጫቸውን ይዘቶች አሠራጭቶ ወይም አስተጋብቶ መገኘት በጥብቅ የተከለከለ ነውም ብሏል። ይህንን መመሪያ ተላልፎ በሚገኝ ማንኛውም ሚዲያ ላይ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ሕጋዊ እና አሥተዳደራዊ እርምጃዎች የሚወስድ መኾኑን አሳስቧል።

#ባሕር_ዳር #መስከረም_11_2019_ዓ_ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article🇪🇹 ከትናንት መሥዋዕትነት እስከ ነገ ተስፋ – ፈተና የማያስቆማት ኢትዮጵያ
Next articleየሰላም ጥሪው ፍሬ ቀጥሏል፤ በፋርጣ ወረዳ ታጣቂዎች ሰላምን መርጠዋል።