🇪🇹 ከትናንት መሥዋዕትነት እስከ ነገ ተስፋ – ፈተና የማያስቆማት ኢትዮጵያ

21

 

የኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ምሥረታ እና ቀጣይነት የትናንት እና የዛሬ ክስተት አይደለም። በዘመናት ቅብብሎሽ ውስጥ በጀግኖች ልጆቿ ደም እና አጥንት፣ በማያወላውል የሀገር ፍቅር ስሜት እና በጽኑ የአንድነት መሠረት ላይ የታነጸ እንጂ።

አፍሪካውያን በቅኝ ግዛት ቀንበር ሥር ወድቀው ማንነታቸውን እና ሀብታቸውን ተነጥቀዋል። በዘመኑ ኢትዮጵያ የራሷን ሉዓላዊነት አስጠብቃ የጥቁር ሕዝብ ሁሉ የነጻነት ተስፋ እና የፀረ-ቅኝ ግዛት ትግል ቀንዲል መኾኗ ዓድዋ ሕያው ምስክር ነው።

የትናንቱ የነጻነት ጽናት ዛሬም አልተቋረጠም። ኢትዮጵያ የገጠሟትን ዘርፈ ብዙ የውስጥ እና የውጭ ፈተናዎች ተቋቁማ የሀገረ መንግሥት ህልውናዋን አጽንታ ቀጥላለች። የኢትዮጵያ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ያለፈውን ታሪክ ጥንካሬዎች በማስቀጠል፣ ስህተቶችን በማረም እና የነገውን ተስፋ በመሰነቅ ላይ የተመሠረተ እንደኾነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያን በልዩነቶቻቸው ውስጥም ቢኾን የሀገር ሉዓላዊነት እና የህልውና አደጋ ሲመጣ በአንድነት የመቆም ታሪካዊ ልምድ አላቸው።

ሉዓላዊነት ማለት ድንበርን ከመጠበቅ ባለፈ በራስ ጉዳይ ላይ በነጻነት የመወሰን፣ የውጭ ጫናዎችን የመቋቋም እና ሀገራዊ ጥቅምን የማስከበር አቅም መኾኑ በኢትዮጵያ ይገለጣል። ኢትዮጵያ ያሳለፈቻቸው የታሪክ ምዕራፎች የሚያስተምሩት ኢትዮጵያ በፈተናዎች ብዛት እንደማትፈርስ፣ ይልቁንም ከችግሮቿ እየተማረች ይበልጥ እየጠነከረች መምጣቷን ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተለያዩ መድረኮች የኢትዮጵያን የማይበገር የሀገረ መንግሥት ጽናት እና የሉዓላዊነት ክብር በጉልህ አስቀምጠዋል። “ኢትዮጵያ እንደ ስንዴ በነፋስ አቅጣጫ የምትወዛወዝ ሳትኾን ሥሯን ጥልቅ አድርጋ እንደተተከለች ዋርካ ናት፤ ቅርንጫፎቿ ሊናወጡ ይችላሉ፣ ግንዱ ግን ጸንቶ ይቆማል፤ ኢትዮጵያ ትፈተናለች እንጂ አትፈርስም፤ ተፈትናም በድል ትሻገራለች” ብለዋል።

“የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት በምንም ዓይነት ሁኔታ ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም። የትናንት አባቶቻችን እና እናቶቻችን በደማቸው ጠብቀው ያስረከቡንን ነጻ እና የከበረች ሀገር እኛም አጽንተን እና አስከብረን ለቀጣዩ ትውልድ እናሻግራለን” ብለዋል። ይህም የሀገረ መንግሥቱ ህልውና ሁልጊዜም ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው መኾኑን የሚያስገነዝብ ነው።

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ የኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥትነት እና የነጻነት ተምሳሌትነት የትናንት ትዝታ ብቻ ሳይኾን የዛሬ ሕያው እውነታ እና የነገ ብሩህ ተስፋ ነው። በየጊዜው የሚገጥሙ ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶች ኢትዮጵያን የትዕግስት፣ የጥበብ እና የአንድነትን ዋጋ እንድትገነዘብ አድርጓታል እንጂ ህልውናዋን አላጠፋውም።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሰመሩበት ኢትዮጵያ የፈተናዎችን ዳገት በእልህ እና በጽናት በመሻገር ዛሬም ኾነ ነገ የነጻነት፣ የኩራት እና የሉዓላዊነት የማይናወጥ ምልክት ኾና በዓለም መድረክ ላይ ደምቃ መታየቷንም ታስቀጥላለች።

AMECO #statebuilding #Ethiopia🇪🇹

#ባሕር_ዳር #መስከረም_11_2019_ዓ_ም

ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleሰላምን አጥብቃችሁ ፈልጓት። 🕊️
Next articleየኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የትግራይ ቴሌቪዥንን አገደ።