
በባሕር ዳር ከተማ “ሰላም ላይ ኢንቨስት እናድርግ ለሁሉም ሰው፣ በሁሉም ቦታ እና በየቀኑ” በሚል መሪ መልዕክት የዓለም የሰላም ቀን ተከብሯል።
የአድማስ ሁለንተናዊ የወጣቶች ዕድገት ማኅበር ሥራ አሥኪያጅ አማረ አድማሱ የዓለም የሰላም ቀን እ.አ.አ በ1981 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በየዓመቱ መስከረም 11 እንዲከበረ ወስኖ መከበር መጀመሩን አንስተዋል።
ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ዕለቱ በየዓመቱ የሰላም መልዕክቶችን በማስተላለፍ፤ ግጨቶች እንዲወገዱ በመሥራት እና ለዓለም ሰላም በመመኘት እየተከበረ መዝለቁን ተናግረዋል።
ዘንድሮ ዕለቱ ዓለም ግጭት ውስጥ ባለችበት ወቅት እየተከበረ መኾኑን ጠቅሰዋል። በዚህም ለሰላም መሥራት አስፈላጊ ኾኗል ብለዋል።
ሰላም የሚመነጨው ከእያንዳንዱ ሰው ነው ያሉት ሥራ አስኪያጁ ግለሰብ ላይ ያለ ሰላም ወደ ቤተሰብ፣ አካባቢ እና ሀገር ይጋባል ነው ያሉት። በዚህም ለሰላም ጊዜያችንን፣ ገንዘባችንን እና ጉልበታችንን ኢንቨስት ማድረግ ይገባናል ነው ያሉት።
በመድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል አካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ፍሬሰላም ዘገዬ የሰላም እጦት ሰዎችን ያፈናቅላል፤ ለአካል ጉዳት ያጋልጣል፤ ሕይወትን ያሳጣል ብለዋል። ግጭት ሀገር የሚያፈርስ መኾኑን ገልጸዋል።
ሰላም ባለመኖሩ ብዙ ነገር አጥተናል ያሉት አቶ ፍሬሰላም ብዙ ሰዎችን በሕይወት ያጣናቸው፤ ብዙዎች አካል ጉዳተኛ የኾኑት፣ ብዙ ልጆች ከትምህርታቸው የተፈናቀሉት፤ ብዙ ሴቶች ለጥቃት የተጋለጡት ሰላምን ከደጃችን በማራቃችን ነው ብለዋል።
ሰላም ከእያንዳንዱ ልብ የሚመነጭ እና ለእያንዳንዱ ዋጋ ያለው ትልቅ ስጦታ መኾኑንም ተናግረዋል። በሀገራችን ሰላም እንዲሰፍን ከሁላችንም አስተዋጽኦ ይጠበቃል ነው ያሉት።
በመድረኩ ሰላም ላይ ትኩረት ያደረገ ጽሑፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
#AMECO #World_Peace_Day #Bahirdar🌴 #ኢትዮጵያ🇪🇹
#ባሕር_ዳር #መስከረም_11_2019_ዓ_ም
ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
