
የሀገር መከላከያ ሠራዊት ለሀገር ሉዓላዊነት እየከፈለ ያለውን መስዋዕትነት የሚደግፍ፣ እንዲሁም የውስጥ እና የውጭ ጠላቶችን እኩይ ተግባር የሚቃወም ሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ በደሴ ዙሪያ ወረዳ ተካሂዷል።
በሰልፉ ላይ የተገኙት የወረዳው ምክትል አሥተዳዳሪ ተስፋዬ አበባው እንደገለጹት መከላከያ ሠራዊት እያደረገ ያለው ተጋድሎ ለሕዝብ ሰላም እና ለሀገር ሉዓላዊነት በመኾኑ የላቀ ክብር ይገባዋል።
ሠራዊቱ ሀገርን ለማፍረስ የሚሠሩ የውስጥ እና የውጭ ጠላቶችን ሴራ በማክሸፍ የኢትዮጵያን አሸናፊነት እያበሰረ የሚገኝ ጀግና ሠራዊት መኾኑን ተናግረዋል።
“የሀገር መከላከያ ሠራዊትን በተለያዩ መንገዶች መደገፍ እና አለኝታነታችንን ማሳየት ያስፈልጋል” ያሉት አቶ ተስፋዬ፤ ይህንንም ከሕዝብ ጋር በመኾን በተግባር እያረጋገጥን እንገኛለን ብለዋል።
አሚኮ ያነጋገራቸው የድጋፍ ሰልፉ ተሳታፊዎችም የሕዝብ ልጅ የኾነው መከላከያ ሠራዊት ሀገርን ለማዳን እያከናወነ የሚገኘውን ተግባር በመደገፍ ሁልጊዜም በጽናት ከጎኑ እንደሚቆሙም አረጋግጠዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
