
የኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ታሪካዊ ጥንካሬውን ከዘመኑ የቴክኖሎጂ ምጥቀት እና ስትራቴጂካዊ ዝግጁነት ጋር አዋሕዶ የሀገርን ሉዓላዊነት እና ደኅንነት በአስተማማኝ ሁኔታ በማስጠበቅ ላይ ይገኛል። ተቋሙ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ባካሄደው ሁለንተናዊ የሪፎርም እና
የመልሶ ግንባታ ሂደት ማንኛውንም ከውስጥም ኾነ ከውጭ የሚሰነዘር ስጋት በብቃት የመመከት አቅሙን ወደ ላቀ ደረጃ አሸጋግሯል።
የሀገር ሕልውና እና የሉዓላዊነት ጽኑ ምሰሶ የኾነው የመከላከያ ሠራዊት ዛሬ ላይ በሰው ኃይል ግንባታ፣ በዘመናዊ ትጥቅ እና በሎጀስቲክስ
ዘመናዊነት አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ከፍቷል። ቀደም ሲል ከነበሩት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር ተቋሙ በዘመናዊ የውጊያ ቴክኖሎጂዎች፣ በአየር ኃይል እና በምድር ኃይል ቅንጅታዊ ክህሎት እንዲሁም በዘመናዊ የላቁ እና የረቀቁ ወታደራዊ ትጥቆች የበለጸገ ቁመና ገንብቷል። ይበልጥ ጎልቶ
የሚታየው ደግሞ በራስ አቅም ወታደራዊ ቁሳቁሶችን እና የሎጀስቲክስ ፍላጎቶችን የማምረት እና የማደራጀት አቅሙ ወደ ከፍተኛ የሥልጣኔ ደረጃ መሸጋገሩ ነው። ይህ የሀገር ውስጥ የማምረት እና የማደስ አቅም የሠራዊቱን የውጊያ ዝግጁነት እና ድል አድራጊነት ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ
አድርጎታል። መሳሪያን በራስ አቅም ከማምረት እና ከቴክኖሎጂ ዝግጅቱ ባሻገር እርሱ የገነባው ወታደራዊ ሥነ-ልቦና እና የዓላማ ጽናት የተቋሙ እውነተኛ ወታደራዊ የበላይነት ምንጭ ነው። የትኛውንም ዓይነት ድንገተኛ ወይም የታቀደ ትንኮሳ በብቃት፣ በቅጽበታዊ ምላሽ እና በላቀ የውጊያ
ስልት መመከት የሚያስችል አዕምሯዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ዝግጁነት ተላብሷል። የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በተለያዩ ሀገራዊ እና ወታደራዊ መድረኮች ያስተላለፏቸው ወሳኝ መልዕክቶችም የዚሁ ጽኑ ወታደራዊ ሥነ-ልቦና
ማረጋገጫዎች ናቸው። “ሠራዊታችን በትጥቅም ኾነ በሥነ-ልቦናዊ ዝግጁነቱ ያለውን አቅም በየጊዜው በማሳደግ ከምንም በላይ ለሀገር ሰላም እና ለሕዝብ ደኅንነት በትኩረት ይሠራል፤ ማንኛውንም ጥቃት ለመመከት ከበቂ በላይ ዝግጁ ነው” ሲሉ ተቋሙ ያካበተውን የውጊያ እና የቴክኖሎጂ
ብቃት ገልጸዋል። የመከላከያ ሠራዊቱ ዋና ዓላማ የሀገርን እድገት እና ብልጽግና ማስቀጠል የሚያስችል አስተማማኝ የሰላም አየር መፍጠር ነው ብለዋል። ወታደራዊ ቴክኖሎጂ እና የኢንዱስትሪ አቅምን ማሳደግ የሀገርን ነጻነት እና ሉዓላዊነት በራስ እግር ላይ ለማቆም የሚደረግ ዘላቂ
ስትራቴጂካዊ እርምጃ ስለመኾኑም አረጋግጠዋል። በአጠቃላይ ይህ በዕውቀት፣ በቴክኖሎጂ እና በላቀ የሥልጠና ጥራት የታነጸ ዘመናዊ ሠራዊት የሀገርን ዳርቻ እና ሰላም የሚያስከብር የብረት ድልድይ ኾኖ አሁናዊ ግዴታውን በቅንጅታዊ እና ስትራቴጅካዊ መንገድ እየተወጣ ይገኛል።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
