“መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሰጣጥ ውጤታማ ተሞክሮዎች የተገኙበት ነው” የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ

11
ቢሮው የ2019 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ በኮምቦልቻ ከተማ እያካሄደ ነው። በመድረኩ የክልል፣ የዞን እና የከተማ አሥተዳደር የሥራ ኀላፊዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲኾን ዋና ዓላማውም ባለፉት ሦስት ወራት የተከናወኑ
ተግባራትን በመገምገም ጠንካራ ጎኖችን ለማስቀጠል እና ያጋጠሙ ክፍተቶችን በጋራ ለመፍታት ነው። በመድረኩ ከተነሱ ዋና ዋና የሪፎርም ስኬቶች መካከል የተቀናጀ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን የሚያረጋግጠው የ”መሶብ” አሠራር በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።
ይህ አገልግሎት የመንግሥት አሠራርን ፈጣን፣ ቀልጣፋ እና ግልጽ በማድረግ የባለጉዳዮችን እንግልት እንደቀነሰ እና እርካታን እንዳረጋገጠ ተመላክቷል። የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኀላፊ ባንችአምላክ ገብረማርያም በሩብ ዓመቱ አበረታች ሥራዎች
መከናወናቸውን ጠቅሰው፣ በመሶብ አገልግሎት አሰጣጥ ውጤታማ ተሞክሮዎች መገኘታቸውን እና አገልግሎቱን ይበልጥ ለማዘመን በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መኾኑን ገልጸዋል። የደቡብ ወሎ ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ አሊ ይማም እና የደሴ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ
ሽመልስ ጌታቸው የመሶብ አሠራር ኅብረተሰቡን ከእንግልት እንደታደገ አንስተዋል።የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ወንደሰን ልሳነወርቅ ከመድረኩ መልካም ተሞክሮ መውሰዳቸውን ገልጸው፣ በከተማዋ እየተገነባ የሚገኘው የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ሕንፃ ግንባታ
በከፍተኛ ፍጥነት እየተከናወነ በመኾኑ በቅርቡ ሥራ ለማስጀመር በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ጠቁመዋል። በመድረኩ በቀጣይ በክልሉ የሚገኙ የሲቪል ሰርቪስ ተቋማትን የአገልግሎት አሰጣጥ ይበልጥ ለማዘመን እና የሰው ሀብት የማስፈጸም አቅምን ለማሳደግ በሚያስችሉ ሀሳቦች ላይ ምክክር እየተደረገም ይገኛል።
✍️በሳሙኤል ኪሮስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“የመከላከያ ሠራዊታችን ከሕዝብ የተወለደ፣ ለሀገር ሉዓላዊነት እና ደኅንነት የሚሠራ የሕዝብ ልጅ ነው” የመካነ ሰላም ከተማ እና የቦረና ወረዳ ነዋሪዎች
Next articleየኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት – በቴክኖሎጂ እና በጠንካራ ሥነ ልቦና የተገነባው የብረት ድልድይ