የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ አቅም እና የዓለም አቀፍ ተደማጭነት ዕድገት።

15

 

ኢትዮጵያ የዓለምን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ ሂደት መዘወር የሚያስችል የብሪክስ አባል መኾኗ የዲፕሎማሲ አቅሟን እና ዓለም አቀፍ ተደማጭነቷን ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገረ ታሪካዊ እርምጃ ኾኗል።

ይህ አባልነት እንደ ቻይና፣ ሩሲያ፣ ሕንድ እና ብራዚል ከመሰሉ የበለፀጉ እና በመበልፀግ ላይ ካሉ ሀገራት ጋር ያለውን አጋርነት በማጠናከር፣ በአፍሪካም ኾነ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተደማጭነት አሳድጎላታል።

🔹የፖለቲካ እና የዲፕሎማሲ ተደማጭነት

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚወሰኑ ዐበይት ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ በውሳኔ ሰጭነት እንድትሳተፍ እና የአፍሪካን ድምጽ አጥብቃ እንድታንጸባርቅ አስችሏታል።

ለዚህ አንዱ መገለጫ በሕንድ ኒው ዴልሂ በተካሄደው 18ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ የብሪክስ አባላት ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅትን ለመቀላቀል የምታደርገውን ጥረት በጽኑ እንደሚደግፉ መግለጻቸው ነው።

የኅብረቱ አባል ሀገራት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ምክር ቤት ተጨማሪ መቀመጫ እንድታገኝ የቀረበውን ሃሳብ ተቀብለዋል።

🔹 የኢኮኖሚ፣ የንግድ እና የፋይናንስ አማራጮች

በአባል ሀገራቱ መካከል የሚደረጉ የንግድ ልውውጦች በሀገር ውስጥ ገንዘቦች እንዲካሄዱ የሚደረገው ጥረት ለኢትዮጵያ የዶላር እጥረትን ለማቃለል ሁነኛ መፍትሔ ነው።

የብሪክስ “አዲስ የልማት ባንክ” ለሀገሪቱ ዐበይት የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች አዲስ የፋይናንስ ምንጭ በመኾን የዜጎችን ሕይወት በማሻሻል ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ያፋጥናል።

ኢትዮጵያ የኅብረቱ አባል መኾኗ የአፍሪካን ጥቅም፣ ፍላጎት እና ድምጽ በብሪክስ መድረክ ላይ አጥብቃ እንድታንጸባርቅ አግዟታል። ለዚህ ሁነኛ ማሳያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን፣ የጸጥታው ምክር ቤትን እና የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማትን አሠራር ፍትሐዊ እና አካታች እንዲኾን ጥያቄዋን እያቀረበች ትገኛለች።

በ18ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ ላይ የተሳተፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እንደገለጹት ኢትዮጵያ ከውጭ የሚገባ ስንዴ ጥገኝነት ሙሉ በሙሉ መውጣቷን ተከትሎ ለታቀደው የብሪክስ የሰብል ልውውጥ ማዕቀፍ በምርት እና አቅርቦት ለመሳተፍ ዝግጁነቷን አሳይታለች።

🔹 የቴክኖሎጂ፣ የኢኖቬሽን እና የሰው ኀይል ልማት።

በዲጂታል መሠረተ ልማት፣ በሰው ሠራሽ አስተውሎት፣ በፋርማሲዩቲካልስ እና ታዳሽ ኢነርጂ ዘርፎች ከተሻሻሉ አባል ሀገራት ጋር የዕውቀት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረላት ይገኛል።

ቀጣይም ኢትዮጵያ አፍሪካን የሚወክል የቴክኖሎጂ አቅም ለመገንባት ከብሪክስ ተቋማት ጋር በጋራ ለመሥራት ፍላጎት እንዳላት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በጉባኤው ማረጋገጣቸው ይታወሳል።

ኢትዮጵያ ወደ ብሪክስ አጋርነት የመጣችው የበኩሏን አስተዋጽኦ ለማበርከት ተዘጋጅታ መኾኑን በጉባኤው ገልጸዋል።

#አሚኮ #ብሪክስ #ኢትዮጵያ🇪🇹

#ባሕር_ዳር #መስከረም_11_2019_ዓ_ም

ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleቢሊየነሮችን የሳበው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ !
Next articleሰላምን አጥብቃችሁ ፈልጓት። 🕊️