ቢሊየነሮችን የሳበው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ !

15

 

ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት እየተከተለችው ያለው ንቁ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ሀገሪቱን የዓለም አቀፍ ባለሀብቶች እና የልማት አጋሮች ማዕከል እያደረጋት ይገኛል።

በተለይም ለኢንቨስትመንት ያሳየችው ቁርጠኝነት እና እየተከናወኑ ያሉ የፖሊሲ ማሻሻያዎች፣ የዓለምን ኢኮኖሚ አቅጣጫ የሚወስኑ ቁንጮ ቢሊየነሮችን ቀልብ በመሳብ ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ አድርጓቸዋል።

ከነዚህ መካከል አፍሪካዊው ስመ ጥር ባለሃብት አሊኮ ዳንጎቴ እና ቢል ጌትስ የሚጠቀሱ ናቸው። የየራሳቸው የኢንቨስትመንት እና የልማት አሻራዎችም በኢትዮጵያ ላይ እያሳረፉ ነው።

​በተለይም ናይጀሪያዊው አሊኮ ዳንጎቴ ኢትዮጵያ ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በመቀጠል ልታሳካው አጥብቃ ትመኘው የነበረውን የማዳበሪያ ፋብሪካ ተስፋ ይዞ ብቅ ያለ ኾኗል። ይህም የኢትዮጵያን የኢኮኖሚው ዘርፍ ዲፕሎማሲ ፍሬ በተግባር የገለጠ ኾኗል።

የዳንጎቴ ግሩፕ ሊቀመንበር አሊኮ ዳንጎቴ ወደ ኢትዮጵያ የሚያደርጉት ተደጋጋሚ ጉዞ ከኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አቅም ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው። በተለይም በኢትዮጵያ እየተገነባ ያለው ግዙፍ የማዳበሪያ ፋብሪካ የኢትዮጵያን የግብርና ምርታማነት በአዲስ መልክ የሚቀይር ስትራቴጂካዊ ፕሮጀክት ነው።

ይህ ፋብሪካ ለአርሶ አደሮች የሚደርሰውን የአፈር ማዳበሪያ እጥረት ከመቅረፍ ባለፈ ሀገሪቱን የግብርና ምርቶች ማዕከል እንድትኾን ያስችላታል። የፕሮጀክቱ መጀመር ኢትዮጵያ በጠነከረ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲዋ የውጭ ባለሃብቶችን መሳብ እንደምትችል እና የቀጣይ እድገቷን ለማረጋገጥ በወሳኝ ምዕራፍ ላይ ለመገኘቷ ማሳያም ነው። ለኢንዱስትሪ መሠረተ ልማት ያላትን ምቹነት እና ለግሉ ዘርፍ የምትሰጠውን ትኩረት ለዓለም የመሰከረም ነው።

​ሌላው የዓለም ቁንጮው ባለሃብት እና በጎ አድራጊ ቢል ጌትስ ወደ ኢትዮጵያ የተሳቡ እና በተደጋጋሚ አዲስ አበባን የረገጡ ወደ ገጠሩም ወጥተው በኢትዮጵያ የስንዴ ማሳዎች ላይ የተመላለሱ ስመ ጥር ሰው ናቸው። ባለሃብቱ ቢል ጌትስ የሚያደርጉት ጉብኝት፣ በዋናነት በዘላቂ ልማት እና በሰው ኃይል ልማት ላይ ያጠነጠነ ነው። ቢል ጌትስ በተለይም በግብርና ምርታማነት፣ በጤናው ዘርፍ እና በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር በአጋርነት የሚሠሩ ኾነዋል።

የእነዚህ ግዙፍ ባለሃብቶች መምጣት በዘፈቀደ የሚከናወን ሳይኾን ውጤታማ በኾነ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ የመጣ ነው። እንደ ዳንጎቴ እና ጌትስ ያሉ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ወደ አዲስ አበባ መምጣታቸው ኢትዮጵያ ደኅንነቷ የተጠበቀ እና ለኢንቨስትመንት ምቹ መኾኗን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ዋነኛ ጠቋሚ ነው።

ይህ ድባብ ሌሎች ባለሀብቶችንም ወደ ኢትዮጵያ በመሳብ፣ የሥራ ዕድል መፍጠር እና የውጭ ምንዛሬን ለማግኘት የሚያስችል በር ይከፍታል።

#አሚኮ #Deplomacy #Ethiopia🇪🇹

#ባሕር_ዳር #መስከረም_11_2019_ዓ_ም

ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“ሁልጊዜም ጥሬ እቃ አቅራቢ ኾነን መቀጠል የለብንም” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)
Next articleየኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ አቅም እና የዓለም አቀፍ ተደማጭነት ዕድገት።