
የአማራ ክልል ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሃብት በአግባቡ ለመጠቀም ልዩ የአመራረት ዘይቤ መከተል እና ኢኮኖሚውን ወደ አንድ ርምጃ ከፍ የሚያደርግ ስልት መቀየስ አስፈላጊ ኾኗል።
ይህን ታሳቢ ያደረገ ምክክር እየተካሄደ ነው። በመድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ እንድሪስ አብዱ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ማዕከል ካደረግን የምንፈልገውን ዕድገት እናገኛለን፣ ይህ ደግሞ የከተሞች ማደግ እና የአኗኗር ዘይቤ ላይ ለውጥ ያመጣል ብለዋል።
የኢኮኖሚ ልዩ ዞን አቅማችን ካደገ ከውጭ የምናገኘውን ምንዛሬ በመጨመር እና ተኪ ምርት ላይ በማተኮር ለውጭ ምንዛሬ ይወጣ የነበረውን ሃብት በከፍተኛ መጠን ይቀንሳል ነው ያሉት።
ይህን ስናደርግ ደግሞ ኢንቨስትመንትን በማቀላጠፍ፣ የሥራ ዕድል በመፍጠር እና ቴክኖሎጂን በማስፋት ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ታላቅ ሚና እንዳለው አንስተዋል።
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን
(ዶ.ር) አማራ ክልል ካለው የሰው ኀይል እና የተፈጥሮ ሃብት አንጻር በቂ የሚባል የአመራረት ዘይቤ አለመኖሩን አንስተዋል።
ክልሉ በተፈጥሮ ሃብት ከፍተኛ ሀገራዊ ድርሻ ቢኖረውም ወደ ምርት ቀይረን ወደ ገበያ የምናወጣበት የእሴት ሰንሰለት የተከተለ አሠራር አልነበረም፣ ይህን ክፍተት ለመሙላት ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ማቋቋም አስፈላጊ ኾኖ ተገኝቷል ነው ያሉት።
የክልሉ አሻጋሪ እድገት እና የዘላቂ ልማት ዕቅድ ትልቁ ሚና መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ችግር ለመቅረፍ ያለመ በመኾኑ ይህን በኢኮኖሚ ልዩ ዞን መምራት ያስፈልጋል ብለዋል።
ሁልጊዜም ጥሬ እቃ አቅራቢ ኾነን መቀጠል የለብንም ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ መሬት ሰጥተን ፋብሪካ ከመገንባት ይልቅ ኢንቨስትመንት፣ ቴክኖሎጂ፣ የሰው ኀይል እና ገበያ መር ኢኮኖሚ በመከተል እሴት የተጨመረበት ኢኮኖሚ መገንባት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ ያለንን ክልላዊ የሰው ኀይል ወደ ሥራ በማስገባት ቴክኖሎጂን እና ኢንቨስትመንትን ማዋሃድ፣ የክልሉን የምርት ዋጋ ማሳደግ፣ እሴት መጨመር እና ወደ ውጭ የሚላክ ጥሬ እቃን አስቀርቶ እሴት የተጨመረበት ምርት መላክ ታላሚ ያደረገ ነው ብለዋል።
እንደ ክልል ይህን ለማሳካት ምቹ ሁኔታዎች አሉን ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ በተለይም ያሉት ነባር የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለልዩ ኢኮኖሚ ዞን ውጤታማነት መነሻ እንደሚኾኑ አንስተዋል።
ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም፣ የክልሉ አሻጋሪ እድገት እና የዘላቂ ልማት ዕቅድ፣ የክልሉን የልማት አቅም በቀጣና ለይቶ ለመጠቀም የያዝነው የትኩረት አቅጣጫ ከምቹ ሁኔታዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።
በተመሳሳይ የዓባይ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ በዚህ ዘርፍ ላይ ለመሰማራት ዋና ዓላማ አድርጎ መግባቱም ለተያዘው የልዩ ኢኮኖሚ ዞን ስኬት ጉዞ መልካም ዕድል ይፈጥራል ነው ያሉት።
እነዚህን ታሳቢ በማድረግ ልዩ የኢኮኖሚ ዞንን ውጤታማ ለማድረግ ባለሃብቶች ወደ ኢንዱስትሪዎች እንዲገቡ እና አርሶ አደሮች ኢንዱስትሪ መር እና ገበያ መር ምርት ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ የመሪዎች ሚና ከፍ ማለት እንዳለበት አሳስበዋል።
በመድረኩ በዓለማቀፍ ደረጃ ያለው የኢኮኖሚ ዞን ልምድ በተለይም የጃፓን፣ ካምቦዲያ፣ ቻይና እና ቬትናም የመሳሰሉ ሀገራት በተሞክሮነት ቀርቧል።
#አሚኮ #ልዩየኢኮኖሚዞን #አማራክልል #ኢትዮጵያ🇪🇹
#አዲስ_አበባ #መስከረም_11_2019_ዓ_ም
ዘጋቢ:- አደራው ምንውዬለት
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
