የኤልኒኖ ተፅዕኖ አሳሳቢ ነውን?

21

 

ባሕር ዳር: መስከረም 11/2019 ዓ.ም (አሚኮ) የዓለም ሜቴዎሮሎጂ ድርጅት ባወጣው መረጃ መሠረት በፓስፊክ ውቅያኖስ የተከሰተው የኤልኒኖ ክስተት በታሪክ ከተመዘገቡት ሁሉ በበለጠ በከፍተኛ ኹኔታ እየጠናከረ ነው።

የውቅያኖስ የሙቀት መጠን መጨመር እና ከክስተቱ ጋር ተያይዞ የሚመጣው አየር ንብረት መዛባት በአፍሪካ ቀንድ በተለይም በኢትዮጵያ ግብርና፣ ውኃ ሃብት እና ምግብ ዋስትና ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ድርጅቱ አስጠንቅቋል።

በመኾኑም የኤልኒኖ ክስተት በታሪክ ከፍተኛው በመኾኑ ይህንን መቋቋም የሚያስችል ዝግጅት ሊኖር እንደሚገባ የፖሊሲ ኢኖቬሽን ምርምር ተቋም ማሳሰቡን ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል።

የኤልኒኖ ክስተቱ በኢትዮጵያ ግብርና እና ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚያሳድርም ተጠቅሷል።

👉ተፅዕኖው ምን ሊያስከትል ይችላል?

​#የሙቀት መጠን መጨመር እና የክስተቱ መጠናከር፦ በአኹኑ ወቅት የተከሰተው የኤልኒኖ ክስተት በታሪክ ከፍተኛው መኾኑ እና ቀደም ሲል ተከስቶባቸው የማያውቁ አዳዲስ ቦታዎችን ጭምር የሚሸፍን ነው ተብሏል።

#በግብርና እና በምግብ ዋስትና ላይ የሚደርስ አደጋ፦ በኢትዮጵያ 30 በመቶ ኢኮኖሚ እና 70 በመቶ የሥራ ዕድል ከግብርና የሚገኝ በመኾኑ በኤልኒኖ ሳቢያ በግብርናው ላይ የሚፈጠረው ተፅዕኖ መላው ኢኮኖሚ ላይ ተፅዕኖው ከፍ ሊል ይችላል።

#በመሠረተ ልማት ላይ የሚደርስ ጉዳት፦ ከግብርናው ዘርፍ በተጨማሪ የኃይል (የኤሌክትሪክ) መሠረተ ልማቶችን ሊጎዳ ይችላል።

#የምርት ማጓጓዝ እና የአቅርቦት ችግር፦ ሀገሪቱ ራሷን የመመገብ አቅም ቢኖራትም ምርትን ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ ለማጓጓዝ የሚያስችል የተመቻቸ ኹኔታ ስጋት ሌላው ሥጋት ተደርጎ ተቀምጧል።

#የተደራረቡ ችግሮች መባባስ፦ ኤልኒኖ ቀደም ሲል መፍትሔ ባላገኙ ሌሎች ነባር ችግሮች ላይ ተደራርቦ ኹኔታዎችን የማባባስ አቅም ሊፈጥር ይችላል።

👉የፖሊሲ ኢኖቬሽን ምርምር ተቋም ያስቀመጣቸው መፍትሄዎች፦

​#የውኃ ማቆር ሥራዎችን መሥራት፣ ነባር ግድቦችን ማጠናከር እና በየቦታው የትናንሽ ግድቦች ግንባታን ማከናወን።

#ባለብዙ ወገን ትብብር እና የማኅበረሰብ ድጋፍ፦ የማኅበረሰብ ድጋፍ ሥራዎችን ከመንግሥት በተጨማሪ የግል ተቋማት እና ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች በጋራ ሊሠሩበት ይገባል።

#የፖሊሲ ማሻሻያ እና የጋራ ቅንጅት፦ ሥራ ላይ ያሉ ፖሊሲዎችን ማሻሻል እንዲኹም ፖሊሲ አውጭዎች እና ተቋማት ለብቻቸው ከመሥራት ይልቅ እርስ በእርስ ተደጋግፈው ሊሠሩ ይገባል።

#በፌዴራል እና በክልል መንግሥታት መካከል ያለውን ትብብር ማሳደግ፣ በተለይም አቅርቦቶችን በማመቻቸት እና በማጓጓዝ በጋራ መሥራት።

#ሀገር አቀፍ የአደጋ ምላሽ ሥርዓት መዘርጋት፦ ክልሎችን ታሳቢ ያደረገ እና አጠቃላይ ሀገራዊ ዝግጁነትን የሚያረጋግጥ የአደጋ ምላሽ መስጫ ሥርዓት መዘርጋትን የመፍትሄ ምክረ ሃሳብ አድርጎ አቅርቧል።

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየመኖ አቅርቦት ችግርን ለመፍታት ምን ተሠራ ?
Next article“ሁልጊዜም ጥሬ እቃ አቅራቢ ኾነን መቀጠል የለብንም” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)