
ባሕር ዳር: ጥቅምት 11/2019 ዓ.ም (አሚኮ) በዘመናዊው ዓለም የሕክምና ሳይንስ እና የቴክኖሎጂ ውህደት ትልቅ አብዮት ፈጥሯል። እንደ አሜሪካ የምግብ እና መድኃኒት አሥተዳደር (Food and Drug Administration – FDA) ገለጻ ዲጂታል ጤና የኮምፒውተር
ሥርዓቶችን እና ሶፍትዌሮችን በመጠቀም የሕክምና አገልግሎትን ማሻሻል ነው። የዲጂታል ጤና ሽፋን በጣም ሰፊ ነው። በስልክ መተግበሪያዎች የጤና መረጃን መከታተልን ያካትታል። የሕክምና ታሪክን በዲጂታል መንገድ ማደራጀትም የዚኹ አካል ነው። የልብ ምትን እና እንቅስቃሴን
የሚያዩ በሰውነት ላይ የሚታሰሩ መሣሪያዎችም ይጠቀሳሉ። በቪዲዮ እና በስልክ ሕክምና ማግኘትም ተችሏል። በሽታን አስቀድሞ ለመመርመር የሚያገለግለው ሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) በስፋት እየተሠራበት ይገኛል።
#ከታካሚዎች እና ከሕዝቡ፦ በሰውነት ላይ የሚታሰሩ ሴንሰሮች (እንደ ስማርት ሰዓት) እና የስልክ መተግበሪያዎች የታካሚውን የልብ ምት፣ የደም ግፊት፣ የስኳር መጠን እና የእንቅስቃሴ መረጃ በቀጥታ ከታካሚው አካል ይሰበስባሉ።
#ከሕክምና ባለሙያዎች እና ከጤና ተቋማት፦ ሐኪሞች በሆስፒታል ውስጥ የሚመዘግቧቸውን የታካሚዎች የካርድ ታሪክ፣ የላቦራቶሪ ውጤቶች እና የምስል ምርመራዎች (X-ray, CT Scan) ወደ ዲጂታል ሥርዓቱ ያስገባሉ።
#በመጨረሻም እነዚህ መረጃዎች በሙሉ በሶፍትዌር እና በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ታግዘው ይተነተናሉ። ይህም ለሕክምና ባለሙያዎች ፈጣን ውሳኔ ለመስጠት ይረዳል። ታካሚዎችም የራሳቸውን የጤና ኹኔታ በስልካቸው እንዲከታተሉ ያደርጋቸዋል።
1.ለሕክምና ባለሙያዎች እና ተቋማት፦
#አላስፈላጊ አሠራርን እና ወጪን ይቀንሳል፦ የሕክምና ባለሙያዎች የታካሚውን ሙሉ የጤና ታሪክ፣ የመድኃኒት አወሳሰድ እና የላቦራቶሪ ውጤቶች በአንድ ቦታ አግኝተው ፈጣን እና ትክክለኛ ውሳኔ እንዲሰጡ ይረዳቸዋል።
#የሕክምና ተደራሽነትን እና ጥራትን ያሳድጋል። ያ ማለት በሩቅ ቦታ ለሚገኙ ሰዎች ሕክምናን ተደራሽ ያደርጋል፤ የአገልግሎት ጥራትንም ያሻሽላል።
#ለእያንዳንዱ ታካሚ እንደራሱ የጤና ኹኔታ እና ፍላጎት የተስማማ ሕክምና ለመስጠት ያስችላል።
2. ለታካሚዎች እና ለሕዝቡ የሚሰጠው ጥቅም፦
#ታካሚዎች ስለራሳቸው የጤና ኹኔታ በቂ መረጃ እንዲኖራቸው እና በጤናቸው ውሳኔ ላይ ንቁ ተሳታፊ እንዲኾኑ ያደርጋል።
#በሽታን አስቀድሞ ለመከላከል እና ለመመርመር ይረዳል። ህይወትን የሚያሰጉ ሥር የሰደዱ ሕመሞችን (እንደ ስኳር እና ደም ግፊት ያሉ) ገና ሳይበራከቱ አስቀድሞ ለመለየት እና ለመከታተል ያስችላል።
#ከሆስፒታል ውጭ ክትትል ለማድረግ ይረዳል። ታካሚዎች ወደ ሕክምና ተቋም ሳይሄዱ ከመኖሪያ ቤታቸው ኾነው የጤና ኹኔታቸውን በስልካቸው ወይም በስማርት መሣሪያዎቻቸው መከታተል እንዲችሉ ያደርጋል።
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይኹኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
