
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አባል የኾኑ አራት ሃይማኖቶች በሰው ልጅ ሰብዓዊ ክብር፣ የአምልኮ ስፍራዎችን ደኅንነት በመጠበቅ፣ ሀገር በቀል የግጭት አፈታቶችን በመጠቀም እና ሴቶች እና ወጣቶችን ለሰላም ተሳታፊ ከማድረግ አንፃር ያላቸውን አስተምህሮ በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።
መግለጫውን የሰጡት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን፣ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል እና የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን ተወካዮች ናቸው። የሃይማኖት አባቶቹ የሁሉም የሃይማኖት
አስተምህሮ ክቡሩን የሰው ልጅ በሰውነቱ ብቻ ያለ ልዩነት እንድናከብር የሚያስተምር እና የሚያዝ ነው ብለዋል። በሰዎች ላይ ማንኛውንም ጥላቻ እና ጥቃት ማድረስ ፈጣሪ ላይ እንደሚደረግ ጥፋት ስለሚቆጠር አስተውሎት በተሞላበት መንገድ መራመድ፣ ሰዎችን መውደድ እና ቤተ
እምነቶች እንደ ራስ መጠበቅ እንደሚያስፈልግም መክረዋል፡፡ ዘመኑ የዲጂታል እንደመኾኑ የቴክኖሎጂ መረቦችን ግጭትን ለመፍጠር እና ለሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ሳይኾን፣ በጎነትን ለማስተማር እና የሕዝብን አንድነት ለመገንባት መጠቀም እንደሚገባም አሳስበዋል።
ሴቶች እና ወጣቶች በሰላም ግንባታ ተሳታፊ እንዲኾኑ መሥራት አስፈላጊ መኾኑን ጠቁመው ሀገርን ለመገንባት ተሳትፏቸውን ማሳደግ ብሎም በጎ ተፅዕኖን ማሳደር ከሃይማኖት አባቶች ይጠበቃል ነው ያሉት። ግጭቶች ሲፈጠሩ ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ሥርዓቶችን በመጠቀም
ልዩነቶችን መፍታት፣ እርቅ መፍጠር እና ማሸማገል ሃይማኖታዊ አስተምህሮው የሚያዝዘው እና ሁሉም አማኝ ሊተገብረው የሚገባ መኾኑንም አስገንዝበዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ቤተልሄም ሰለሞን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
