
በደሴ ከተማ በወተት ላም እርባታ ዘርፍ ተሠማርተው የሚገኙት ወይዘሮ ፀሐይነሽ ግዛው የጽናት እና የስኬት ምሳሌ ናቸው። ሥራውን የጀመሩት በአንድ ወተት ላም እና በ20 ሺህ ብር ብቻ እንደነበር አስታውሰዋል። ዛሬ ላይ የላሞቻቸውን ቁጥር በማሳደግ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል። ካፒታላቸውንም 18 ሚሊዮን አድርሰዋል። በጥራት የወተት ምርትን ለማኅበረሰቡ በማቅረብ ትልቅ ድርጅት መገንባት ችለዋል።
በረጅም ዓመታት ጉዟቸው ታድያ ስኬት ብቻ ሳይኾን ፈተናዎችንም አሳልፈዋል። ይህንንም በጽናት አልፈዋል። ከእነዚያ ፈተናዎች ውስጥ የመኖ ዋጋ ውድነት እና እጥረት አሁንም በዘርፉ ላይ ትልቁ ፈተና ኾኖባቸው እንደቀጠለ ተናግረዋል። ይሁንና ለችግር እጅ ሳይሰጡ የራሳቸውን የግል መኖ በማዘጋጀት ፈተናውን በመቋቋም ላይ እንደሚገኙ ነው የተናገሩት።
ዘርፉ በርካቶችን ውጤታማ ማድረግ የሚችል መኾኑን ያነሱት ወይዘሮ ፀሐይነሽ ለመኖ ችግር ግን ዘላቂ መፍትሔ መስጠት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሣ ሀብት ልማት ቢሮ የእንስሳት ተዋጽኦ እና መኖ ልማት ዳይሬክተሩ መኳንንት ዳምጤ ዘርፉን ሳይንሳዊ በማድረግ የሰው ኃይል አቅምን በማሳደግ እና ቴክኖሎጂዎችን በወቅቱ በማቅረብ ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ የማድረግ ሥራዎች እየተሠሩ እንደኾነ ገልጸዋል።
በኩታ ገጠም ሞዴል መንደር በመፍጠር ወጣቶችን በሼዶች የማደራጀት ሥራ መሠራቱን ነው የተናገሩት። የመሬት ብድር እና ሌሎች ችግሮችን ከአጋር አካላት ጋር በጋራ ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
በዘርፉ ትልቁ ማነቆ የኾነውን የመኖ አቅርቦት ችግር ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መኾኑንም አንስተዋል። በዘርፉ የተሠማሩ ግለሰቦች በውል እርሻ አረንጓዴ መኖን በስፋት የማልማት ሥራ ተጀምሯልም ብለዋል።
መንግሥት በክልሉ በዋና ዋና ከተሞች ጎንደር፣ ደሴ፣ ኮምቦልቻ፣ ባሕር ዳር እና በሌሎችም በሰዓት 7 ሺህ ኪሎ ግራም መኖ መቆራረጥ የሚችሉ ስድስት ዘመናዊ የገፈራ ቴክኖሎጂዎችን አቅርቧል ነው ያሉት። በዚህም በአነስተኛ ወጪ ተጠቃሚ እየኾኑ ነው ብለዋል።
የሰብል ተረፈ ምርት ምርታማነትን በማሳደግ እና በወቅቱ በመሠብሠብ እንዲጠቀሙ የማድረግ ሥራም እየተከናወነ መኾኑን ገልጸዋል። የተመጣጠነ ገፈራ እና የተሻሻለ መኖ በማዘጋጀት ወደ ተግባር በመገባቱ የወተት ምርት እያደገ መጥቷል ነው ያሉት።
በዘርፉ ጥራት ያለው የወተት እና ሥጋ ምርት እየተመረተ ነው ብለዋል። ባለፈው ዓመትም በወተት፣ በእንቁላል እና በዓሣ ሀብት ዘርፎች የተሻለ አፈጻጸም መመዝገቡን አንስተዋል። በቀጣይም የማኅበረሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተቀናጀው የልማት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ያስረዱት።
#አሚኮ #እንስሳት_ሀብት #ኢትዮጵያ 🇪🇹
#ባሕር_ዳር #መስከረም_11_2019_ዓ_ም
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
