የሰላም አማራጩ ተጨባጭ ውጤት እያሳየ ነው።

6

 

ላለፉት ሦስት ዓመታት በርካታ ወጣቶች በትጥቅ ትግል ውስጥ በመሳተፍ ሕይወታቸውን በከንቱ ማጣታቸውን በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ገልጸዋል። በተሳሳተ መንገድ ነፍጥ አንግበው በመውጣታቸው እንታገልልሀለን የሚሉትን ሕዝብ ለማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ሲዳርጉትም ቆይተዋል።

በዚህም ምክንያት ባለሃብቶች በደኅንነት ስጋት ቀየ እና ልማታቸውን ትተው ሲሸሹ እንደነበርም የሚታወስ ነው።

ላለፉት ሦስት ዓመታት መንገድ በመዝጋት፤ የባለሃብት መኪና ከነጭነቱ በማቃጠል፤ ሹፌሮችን በመግደል እና ተሳፋሪዎችን በማገት ከአማራ ሕዝብ ባሕልና እሴት ያፈነገጠ ግፍ ተፈጽሟል ነው ያሉት ነዋሪዎቹ።

ይህ ድርጊት አርሶ አደሮች ምርታቸውን ወደ ገበያ እንዳያጓጉዙ በማድረግ፣ በምርቶች ላይ የዋጋ ንረት እንዲጨምር በማድረግ፣ የምርት አቅርቦት እጥረት እንዲከሰት እና የኑሮ ውድነት እንዲባባስ ምክንያት ኾኖም ቆይቷል።

ይሁን እንጂ በራስ ሕዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ይህን መጥፎ ድርጊት የተረዱ በርካታ ወጣቶች የመንግሥትን የሰላም አማራጭ ተቀብለው እየገቡ ይገኛሉ። በሰሜን ጎንደር፣ በምዕራብ ጎንደር፣ በደቡብ ጎንደር፣ በሰሜን ወሎ እና በምዕራብ ጎጃም አካባቢዎች የሚገኙ በርካታ የታጠቁ ኃይሎች ጥሪውን ተቀብለው ወደ ሰላማዊ ሕይወት ተመልሰዋል።

የመንግሥት የሰላም አማራጭ በጫካ የነበሩ ታጣቂዎች በሰላም ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ትልቅ ዕድል መፍጠሩን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።

“ዓላማ በሌለው ትግል ተሰልፈን ያሳደገንን እና ያስተማረንን ማኅበረሰብ ዕረፍት መንሳት የለብንም” በማለት ትጥቃቸውን ፈትተው ወደ ሰላም መጥተዋል። የወጣቶች የሰላም እርምጃም በክልሉ አንጻራዊ ሰላም እንዲሰፍን አስችሏል።

በዚህ የሰላም አማራጭ በተከፈተው ዕድል በአካባቢያቸው መደበኛ ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፤ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ዘርፉም መነቃቃት አሳይቷል ነው ያሉት ነዋሪዎቹ።

የሰላም አማራጩ ወጣቱን ከእርስ በርስ ግድያ ከመታደግ እና የሰላምና ልማት ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ፣ በክልሉ ተጨባጭ የሰላም ውጤት እንዲመጣ አድርጓልም ብለዋል።

የሕዝቡ ዋነኛ ችግር የኾነውን የጽንፈኝነት አስተሳሰብ በመታገል ምቹ ከባቢ መፍጠር እንደሚገባ በአንድ ወቅት የገለጹት ደግሞ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ናቸው።

በተለይም ፍላጎትን በኃይል ለማስመለስ የታጠቀ የጽንፈኝነት ኃይል ስላለ ይህንን መታገል ዋነኛ ሥራ መኾን እንዳለበትም ገልጸዋል።

አሁን ያለውን ሰላም ማጠናከር፤ የጸጥታ ኃይሉን የበለጠ ማገዝ እና ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባም ማሳሰባቸው ይታወሳል።

#አሚኮ #peace #Ethiopia

#ባሕር_ዳር #መስከረም_11_2019_ዓ_ም

ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየጥላቻ ንግግር እና መዘዙ፦