🕊️ ታጣቂዎች መሣሪያቸውን አስቀመጡ፤ የሕዝብ የሰላም ምኞትም ሰመረ 👏

66

 

ሰሜን ጎንደር ዞን ከ 2015 ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ የተፈጠረው ግጭት ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ካደረሰባቸው አካባቢዎች መካከል አንዱ ነው። በግጭቱ የዞኑ ማኅበረሰብ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴም በከፍተኛ ሁኔታ ታውኮ ቆይቷል።

በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች እንደሚሉት ያለፉት ሦሥት የግጭት ዓመታት እንደ ማኅበረሰብ ከፍተኛ ዋጋ አስከፍለዋል። በታጣቂዎች በሚፈጸሙ እገታዎች፣ ዘረፋዎች፣ እና ግድያዎች ከዞኑ መቀመጫ ደባርቅ ወደ ጎንደር፤ ወደ አዳርቃይ፣ ጠለምት፣ ጃናሞራ እና በየዳ ለመጓዝ አስቸጋሪ ነበር ብለዋል። ለንግድ ልውውጥ፣ ለሐዘን እና ለደስታ ለመንቀሳቀስ ተቸግረን ነበርም ይላሉ።

ነዋሪዎቹ እንደሚሉት በቅርቡ በዞኑ ይንቀሳቀሱ የነበሩ በርካታ ታጣቂዎች የሕዝብን ጩኸት ሰምተው የሰላም አማራጩን እየተቀበሉ በመኾናቸው በማኅበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ደስታን ፈጥሯል። ዘላቂ ሰላም እንደሚሰፍንም ሙሉ ተስፋ አለን ብለዋል። አሁን ላይም ማኅበረሰቡ ያለምንም ሰቀቀን ከደባርቅ ወደ ሁሉም የዞኑ ወረዳዎች የሚንቀሳቀስበት ሁኔታ እየፈጠረ ነው።

ነዋሪዎቹ የተሟላ እርቅ ተፈጽሞ መንግሥት እና ታጣቂዎች ተግባብተው ለሕዝብ የሚጠቅም ሥራ እንዲሠሩ የማኅበረሰቡ ፍላጎት መኾኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል። ታዲያ የተሟላ ሰላም እንዲረጋገጥ ከሰሜን ጎንደር ዞን ባለፈ በአጎራባች ዞኖች የሚገኙ ታጣቂዎችም የሰላም አማራጩን ሊቀበሉ እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት።

የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ዲያቆን ሸጋው ውቤ ታጣቂዎቹ በነበሩባቸው አካባቢዎች ሕዝብን የሚያሳቅቁ የእርስ በእርስ ግጭቶች፤ እገታዎች እና ዝርፊያዎች ይፈጸሙ እንደነበር አንስተዋል።

አሁን በዞኑ የሚንቀሳቀሱ በርካታ ታጣቂዎች የሰላም አማራጩን እየተቀበሉ መኾናቸውንም ተናግረዋል።

አሥተዳዳሪው እንደሚሉት የታጣቂዎች በስፋት የሰላም አማራጩን መቀበላቸው በርካታ ዕድሎችን ፈጥሯል።

✅ ታጣቂዎቹ ይገኙባቸው በነበሩ አካባቢዎች ማንኛውንም የልማት ሥራ ማከናወን የሚቻልበት እንዲኹም ማኅበረሰቡ ማንኛውንም መስተጋብሮች በነጻነት እንዲከውን ዕድል ፈጥሯል።

✅ ታጣቂዎቹ በነበሩባቸው አካባቢዎች ሁሉም ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ እና ለመማር ማስተማር ዝግጁ እንዲኾኑ ተደርጓል።

✅ ሁሉም የዞኑ የመንግሥት መዋቅር በየቀበሌዎቹ በተደራጀ መልኩ ተከፍተው ሕዝቡ አገልግሎት እንዲያገኝ እየተደረገ ነው።

✅ የመንግሥት ተቋማት እና አስፈጻሚዎች በነጻነት ተንቀሳቅሰው ሥራ እንዲሠሩ ዕድል ፈጥሯልም ብለዋል።

✅ማኅበሰቡም ከነበሩት እገታ፣ ዝርፊያ እና ግድያ ነጻ ኾኖ ማኅበራዊ ሕይወቱን የሚከውንበት ዕድል ተፈጥሯል።

በርካታ ታጣቂዎች የሰላም ጥሪውን እየተቀበሉ መኾናቸው በዞኑ ማኅበረሰብ ዘንድ ደስታ እና ተስፋን የሰጠ ከመኾኑም በላይ ከፍተኛ የሰላም አየር እየነፈሰ ነው ብለዋል።

#አሚኮ #የሰላምአማራጭ #ሰላም #ኢትዮጵያ 🍃 🇪🇹

#ባሕር_ዳር #መስከረም_07_2019_ዓ_ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየባሕር በር ጉዳይ በሰጥቶ መቀበል ዲፕሎማሲያዊ መርህ እልባት እንዲያገኝ የምሁራን ጥረት ወሳኝ ነው።
Next articleበምዕራብ ጎጃም ዞን ባለፈው በጀት ዓመት ምን ተሠራ?