
በምሥራቅ ጎጃም ዞን የትምህርት አጀማመር ላይ ትኩረት ያደረገ የውይይት መድረክ በደብረ ማርቆስ ከተማ ተካሂዷል። በመድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ጥላሁን ወርቅነህ በዘንድሮው የትምህርት ዘመን በግጭት ምክንያት ከትምህርት ገበታ ርቀው የነበሩ
ታዳጊዎች ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመለሱ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማሌዎች ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መኾኑን አንስተዋል።
ኀላፊው የትምህርት ሥርዓቱን ሀገር በቀል ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። የትምህርት ቤቱ ማኅበረሰብ እና እያንዳንዱ ዜጋ ሰላማዊ
የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር የበኩሉን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል። የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ዋለ አባተ እንዳሉት በዞኑ የሚገኙ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታቸው ለመመለስ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመተባበር የመምህራንን ሥነ ልቦና የመመለስ እና የወላጆችን ተሳትፎ የማስደግ ተግባር ተከናውኗል።
ዋና አሥተዳሪው ግብረ ሰናይ ተቋማት ድጋፍ እና እገዛ እንዲያደርጉ በማበረታታት ዞኑን ወደ ቀደመ ተወዳዳሪነቱ መመለስ ይገባልም ብለዋል።
በመድረኩ ከዞኑ ሁሉም ወረዳዎች የተውጣጡ የትምህርት መሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች የትምህርት ሥርዓቱ እና የተማሪዎች ተሳትፎን ለማሻሻል የሀገር ሽማግሌዎች እና አባቶች የሠሩት ሥራ የሚበረታታ መኾኑን ገልጸዋል።
ትምህርት ተደራሽ ባልኾነባቸው አካባቢዎች ላይ ለመድረስ ከማኅበረሰቡ ጋር በጥምረት እየተሠራ ነውም ብለዋል።
አሚኮ ያነጋገራቸው በመድረኩ የተሳተፉት የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ተተኪ ትውልድን ለማፍራት በሕጻናት ላይ መሥራት እና በትምህርት አንፆ ማሳደግ ያስፈልጋል ብለዋል። ለዚህም የድርሻቸውን ለማበርከት እየሠሩ መኾናቸውን አረጋግጠዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
