
የአዲስ አበባ አመራር አካዳሚ የናይል ወንዝ እና የባሕር በርን አስመልክቶ የፓናል ውይይት አካሂዷል። “የኢትዮጵያ የባሕር በር ጉዳይ በምሁራን ዕይታ” በሚል መሪ መልዕክት በቀረበው የፓናል ውይይት የዘርፉ ተመራማሪዎች ተወያይተዋል።
የአዲስ አበባ አመራር አካዳሚ ፕሬዝዳንት ጣሰው ገብሬ (ዶ.ር) የባሕር በር ጉዳይ ከዕለታዊ የፓለቲካ ጉዳይነት ባለፈ የቀጣናው የኢኮኖሚ ትስስር እና ትብብር ጉዳይ መኾኑን መረዳት ይገባል ብለዋል።
አካዳሚው በምርምር የተገኙ ምክረሃሳቦችን ወደ ሕዝቡ ለማድረስ እና የጋራ መፍትሔ ለማስቀመጥ ምሁራኑ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ታልሞ መድረኩ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር ጋር ጠንካራ ታሪካዊ ዳራ ያላት ሀገር በመኾኗ የህልውና ጉዳይ መኾኑን መረዳት እና ተገቢውን ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ተብራርቷል።
በመድረኩ ለንግድ፣ ለሎጅስቲክ፣ ለኢኮኖሚ እና ብሔራዊ ደኅንነት ቀጥተኛ ጠቀሜታ ያለው ቀይ ባሕር በዲፕሎማሲያዊ ጥረት እንዲመለስ ምሁራን ዕውቀት እና ሃሳባቸውን ማዋጣት አለባቸው ነው የተባለው።
በመድረኩ የተገኙት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በዜግነት የምንጋራው የወቅቱ አጀንዳ የኾነው የባሕር በር ጉዳይ በሰጥቶ መቀበል ዲፕሎማሲያዊ መርህ እንዲገኝ ምሁራን መሰል መድረኮች ላይ በንቃት መሳተፍ አለባቸው ብለዋል።
በሕዳሴ ግድቡ የታየው አይነት የሕዝብ አንድነት በባሕር በርም መደገም እንዳለበት አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ብሔራዊ አጀንዳ እንዲሳካ ምሁራን ዲፕሎማሲያዊ አማራጮችን በማመላከት ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ተገልጿል።
#አሚኮ #የባሕርበር #ኢትዮጵያ 🍃 🇪🇹
#አዲስ_አበባ #መስከረም_07_2019_ዓ_ም
ዘጋቢ:- ቤተልሄም ሰለሞን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
