
በደሴ ከተማ ነዋሪ የኾነችው ወጣት መቅደስ መሠለ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አስደናቂ የልጆች ቦርሳ ሠርታ ለገበያ አቅርባለች።
አሚኮ ከአልማ ጋር በትብብር ባዘጋጀው የብቁ ወጣት ውድድር ላይ ነበር መቅደስ ይህንን ድንቅ የፈጠራ ሥራዋን ያቀረበችው።
መቅደስ በዚህ ወቅት እንደተናገረችው የዕደ ጥበብ ሥራን ከአባቷ ቀስማለች። ይህንን የአባቷን የጥበብ ውርስ እርሷ ከደረሰችበት የቴክኖሎጂ ዘመን ጋር አዋህዳ እና በቴክኖሎጂ አሳድጋ ማምረት ችላለች።
አብዛኞቹ ቦርሳዎች የሀገርን ባሕል ያላገናዘቡ በመኾናቸው በሕጻናት ላይ የውጭ ባሕል ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ ትናገራለች። በዚህም ልጆች በቀላሉ የሌላ ሀገርን ባሕል በአዕምሯቸው እንዲቀረጽባቸው ተጽዕኖ እንደሚፈጥር ትገልጻለች። ይህንን ችግር ለመቅረፍ ወደ ሥራው መግባቷንም አስረድታለች።
📌 የቦርሳው ልዩ ባህሪያት እና ጥቅሞች፦
ወጣት መቅደስ እንደገለጸችው በፈጠራ ሥራዋ ያቀረበችው ቦርሳ ከተለመደው ቦርሳ ያደገ፣ የቆዳ ውጤት የኾነ፣ የባር ኮድ (QR Code) ያለው፣ መተግበሪያዎችን (Applications) መጠቀም የሚችል ዘመናዊ ቦርሳ ነው።
በቦርሳው የተገጠመለት ባር ኮዱ ስካን ተደርጎ መተግበሪያዎች ሲከፈቱ በቦርሳው ላይ ያለውን ነገር ማሳየት ይችላል። በዚህ ቴክኖሎጂ የሀገር ባሕልን፣ አብሮ መብላትን፣ አብሮ መጠጣትን የሚያሳዩ ቪዲዮዎችን ማሳየት ይችላል ብላለች።
ይህም በውጭ የተቀናበሩ የሕጻናት ካርቶኖችን ከማሳየት በመውጣት ሕጻናት ተማሪዎች የሀገር ውስጥ ባሕልን እና ማንነትን መሠረት ያደረጉ የአብሮነት ምስሎችን የሚያቀርብ ዓላማ ያደረገ ስለመኾኑም አብራርታለች።
በቀጣይም GPS የእንደሚገጠምለት እና ወላጆች የልጆቻቸውን ደኅንነት ከቤታቸው ኾነው ለመከታተል የሚያስችሉ መረጃዎችን እና ሌሎች ሥርዓቶች እንደሚካተቱበትም ጠቁማለች።
🎒 የጥራት ደረጃ፦ ከተለመደው ቦርሳ ያደገ፣ የቆዳ ውጤት የኾነ እና ለሕጻናት በሚስብ መልኩ የተዘጋጀ ቦርሳ ነው። ከትላልቅ ቦርሳዎች በተጨማሪም በትናንሽ የኪስ ቦርሳዎች (ዋሌት) ጭምር እንደሚያመርቱም ተናግራለች። በዚህም ለውጭ ቱሪስቶች ተመራጭ እና ተወዳጅ እንደሚኾን ነው የገለጸችው።
💰 ዋጋ እና የካፒታል ፍላጎት፦
ይህንን ድንቅ ቦርሳ በአሁኑ ወቅት በ1 ሺህ ብር ብቻ ለማኅበረሰቡ በማቅረብ ላይ እንደሚገኙ ነው የተናገረችው። ቦርሳውን በውጭ ገበያ ደረጃ በጥራት አምርቶ ለማቅረብ ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልጋት ወጣት መቀደስ ገልጻለች።
#አሚኮ #Inovation #ኢትዮጵያ🇪🇹
#ባሕር_ዳር #መስከረም_06_2019_ዓ_ም
✍️በአሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
