“ተማሪዎች ውጤታማ እንዲኾኑ ሁሉም ሊያግዝ ይገባል” ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)

3
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) እና የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የሥራ ኀላፊዎች በባሕር ዳር ከተማ በተለያዩ ትምህርት ቤቶች በመገኘት የ2019 ዓ.ም የትምህርት አጀማመርን ተመልክተዋል።
ዶክተር ሙሉነሽ ደሴ በዚህ ወቅት እንዳሉት ከነሐሴ/2018 ዓ.ም ጀምሮ ምዝገባ ሲካሄድ መቆየቱን ተናግረዋል። እስከ መስከረም 04/2019 ዓ.ም ድረስ 4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ተማሪዎች መመዝገባቸውንም ገልጸዋል። ከመስከረም 05/2019 ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ የመማር ማስተማር ሂደት መጀመሩንም ነው ያነሱት።
የትምህርት ዘመኑ እና ተማሪዎች ውጤታማ እንዲኾኑ ማኅበረሰቡ፤ መምህራን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ኀላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ተናግረዋል።
ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣም አሳስበዋል። ባለፉት ዓመታት በጸጥታ ችግር ምክንያት ተቀዛቅዞ የነበረው የትምህርት አጀማመር ሂደት መነቃቃት ማሳየቱንም ገልጸዋል።
ያልተመዘገቡ ተማሪዎች በቀጣይ እንዲመዘገቡ እና በትምህርት ገበታ ላይ እንዲገኙ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣም ጥሪ ቀርቧል።
በጉብኝቱ ወቅት አሚኮ ያነጋገራቸው የትምህርት ቤት ርእሰ መምህራን እና ተማሪዎች በወቅቱ ትምህርታቸውን መጀመራቸውን ገልጸዋል።
የተመዘገቡ ተማሪዎች ከሌሎች ዓመታት በተሻለ መልኩ በትምህርት ጅማሮ ላይ መገኘታቸውንም ጠቁመዋል።
ተማሪዎችን ቀድሞ በመመዝገብ፣ በወቅቱ ትምህርት በማስጀመር እና መምህራን ክፍለ ጊዜን በአግባቡ ተጠቅመው እንዲያስተምሩ በማድረግ በልዩ ትኩረት የመማር ማስተማር ሂደት መጀመሩንም አንስተዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“ሕዝብ ያመነባቸው ተጨባጭ ስኬቶች ተመዝግበዋል” አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር)