
የአማራ ክልል የአሥተዳደር ክላስተር ተቋማት የ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2019 በጀት ዓመት የሥራ ትውውቅ መድረክ አካሂደዋል።
በመድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ.ር) በ2018 በጀት ዓመት የሕዝባችን ሰላም እና ደኅንነት ለማስጠበቅ፤ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር እና የተጋረጠውን ዘርፈ ብዙ የጸጥታ ሁኔታ ለመሻገር በርካታ ጥረቶች መደረጋቸውን አንስተዋል።
የሕግ የበላይነትን ለማስከበር እና የሕዝብን ሰላም ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራትም የላቀ ስኬት ተመዝግቧል ነው ያሉት። ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት ነው፤ ያለሰላም የሚታሰብ ልማት እና የመልካም አሥተዳደር ግንባታ የለም ብለዋል። በመኾኑም የጸጥታ መዋቅሩ በተጠናከረ ሙያዊ ሥነ ምግባር እና ሕዝባዊ ወገንተኝነት ሰላምን ማጽናት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕርግ የአሥተዳደር ዘርፍ አሥተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር) ባለፈው በጀት ዓመት በርካታ ፈተናዎች ቢገጥሙም በልማት፣ በሰላም እና ጸጥታ ተግባራት ሕዝብ ያመነባቸው ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
መሪዎች በአንድ በኩል ልማትን እያረጋገጡ በሌላ በኩል ደግሞ ሰላምን እያስጠበቁ የቆዩበት ዓመት ነበር ብለዋል። በክልሉ የሚገኙ ጽንፈኛ ኃይሎች ከታሪካዊ ጠላቶች ጋር ጥምረት በመፍጠር የሕዝብን ሰላም እና ልማት ለማደናቀፍ የሚችሉትን ሁሉ ሞክረዋል፤ ይሁን እንጅ በሀገር መከላከያ ሠራዊት፤ በክልሉ የጸጥታ መዋቅር፤ በመሪዎች እና በሕዝቡ የተቀናጀ ጽኑ ትግል ህልማቸውን ማምከን ተችሏል ብለዋል።
ለክልሉ ሰላም እና ልማት መረጋገጥ ከትናንት በተሻለ መልኩ ነገን መገንባት ይጠበቅብናል ነው ያሉት። የአማራ ሕዝብ ከጸጥታ መዋቅሩ የሚጠብቀው ሰላምን፣ ደኅንነትን፣ ፍትሕን እና ታማኝነት ያለው የመንግሥት አገልግሎትን ነው ያሉት ዶክተር አማኑኤል የጸጥታ እና የአሥተዳደር ተቋማት በተቀናጀ እና በተደራጀ መንገድ ተግባራትን መፈጸም አለባቸው ብለዋል።
በቀጣይ ክልሉ ሰላም እና ደኅንነት የተረጋገጠበት፣ ፍትሕ የሰፈነበት እና ሕዝባዊ ታማኝነት ያደገበት አገልግሎት ለመስጠት የጸጥታ መዋቅሩ በቁርጠኝነት እና በጽናት መታገል እንደሚገባውም አሳስበዋል።
ዘጌቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
