
ታሪካዊቷ ደብረ ማርቆስ ከተማ ለኢንቨስትመንት የተመቸች፣ አያሌ ጸጋዎችን አቅፋ የያዘች ናት። ይህችን ከተማ በኢንቨስትመንት ዘርፉ የተሻለ ደረጃ ለማድረስ እየተሠራ ነው።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተሾመ ዋለ ባለፉት ዓመታት የነበረው የጸጥታ ችግር በኢንቨስትመንት ዘርፉ ተጽዕኖ ፈጥሮ መቆየቱን አስታውሰዋል። የጸጥታ ችግሩ አካባቢውን ባለሃብቶች ለቅቀው እንዲሄዱ እና ከኢንቨስትመንት ዘርፉ ሊገኝ ይችል የነበረው ገቢ እንዲቀንስ አድርጎ መቆየቱንም አንስተዋል።
አሁን ላይ ግን በተገኘው ሰላም የኢንቨስትመንት ዘርፉ እየተነቃቃ መኾኑን ገልጸዋል። በከተማ አሥተዳዳሩ 222 በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች እንዳሉም ተናግረዋል።
በኢንዱስትሪ ዘርፉ የተሠማሩ ባለሃብቶች አብዛኛዎቹ በልማት ላይ መኾናቸውንም ገልጸዋል። ለአብነት በከተማዋ የሚገኘው የማኛ ጤፍ ማቀነባበሪያ ትርፍ አምራች የኾኑትን የአካባቢውን አርሶ አደሮች ተጠቃሚ የሚያደርግ፣ ጤፍን ወደ ውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝ መኾኑን ተናግረዋል።
ደብረ ማርቆስ ከተማ በማዕድን፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ እና በሌሎች ዘርፎች ለሚሠማሩ ባለሃብቶች ምቹ መኾኗን ገልጸዋል። የከተማዋን ጸጋ ታሳቢ ያደረገ ዕቅድ በማቀድ የኢንቨስትመንት ፍሰቱን ለመጨመር እየተሠራ ነውም ብለዋል።
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አማካኝነት በጸጥታ ችግር ምክንያት ሥራ አቁመው የነበሩ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ መግባታቸውንም ገልጸዋል። በግንባታ ላይ ያሉት ወደ ሥራ እንዲገቡ፣ ተጨማሪ አዳዲስ እንዱስትሪዎችም ወደ ከተማዋ እንዲመጡ እየሠራን ነው ብለዋል።
የከተማ መጨረሻ መዳረሻው ዘመናዊነት እና ኢንዱስትሪ ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ኢንቨስትመንት ሰላምን ይፈልጋል፤ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ አስተማማኝ ሰላምን መፍጠር ያስፈልጋል ነው ያሉት። አሁን ላይ የከተማዋ ሰላም የተጠበቀ መኾኑንም ገልጸዋል።
ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ደግሞ ሁሉንም የሰላም ባለቤት የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል። የደብረ ማርቆስ ንጉሥ ተክለሃይማኖት አውሮፕላን ማረፊያ አገልግሎት መጀመሩ ከተማዋ እንድትነቃቃ እያደረገ መኾኑን ገልጸዋል። የሆቴሎች፣ የከተማዋ የንግድ እንቅስቃሴ እና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴው እንዲነቃቃ ማድረጉንም ተናግረዋል። የአውሮፕላን ማረፊያው ለዓመታት ሲጠበቅ የነበረውን ፍሬ እየሰጠ መኾኑንም ገልጸዋል።
ደብረ ማርቆስ እና አካባቢው በቱሪዝም ጸጋ የታደለ ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ሰላምን ከዚህ በላይ ማረጋገጥ እና አስተማማኝ ማድረግ የቱሪዝም እንቅስቃሴው እንዲያድግ ያደርጋል ብለዋል። ለከተማዋ መልማት የሕዝቡ ተሳትፎ ትልቅ መኾኑንም ገልጸዋል።
ባለሃብቶች ወደ ከተማ ለኢንቨስትመንት ሲመጡ ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት በቴክኖሎጂ የተደገፈ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።
ከአሁን ቀደም የነበረው አገልግሎት አሰጣጥ ውስንነት ነበረው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የቀደመውን የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተት የሚያስቀር ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ባለሃብቶች ለኢንቨስትመንት እንዲመጡ አገልግሎት ወሳኝ መኾኑን ገልጸዋል። ባለሃብቶች አልምተው በከተማዋ ዕድገት ላይ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉም በትኩረት እንደሚሠራ ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
