‎ከስጋት ወደ ልማት – የምሥራቅ ጎጃም ዞን አዲስ የኢንቨስትመንት ምዕራፍ

7
🏭
‎የምሥራቅ ጎጃም ዞን በኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በግብርና እና በሌሎች የልማት ዘርፎች ጸጋ ያለው አካባቢ ነው። ‎በዞኑ ከሚገኙ ትልልቅ ኢንዱስትሪዎች መካከል በደጀን ከተማ እየተገነባ የሚገኘው የዓባይ ሲሚንቶ ፋብሪካ ፕሮጀክት አንደኛው ነው።
‎‎የዓባይ ሲሚንቶ ፋብሪካ ፕሮጀክት ሥራ አሥኪያጅ ኢንጂነር አስራት ኪዳኑ የዓባይ ሲሚንቶ ፋብሪካ በጥሩ ሂደት ላይ መኾኑን ገልጸዋል። የጥሬ ዕቃ ማከማቻዎች፣ የሰሚንቶ ማቀነባበሪያው እና ሌሎች ሥራዎች በጥሩ አፈጻጸም ላይ መኾናቸውን ተናግረዋል።
‎በፋብሪካው የሚገጠሙ ማሽኖች በመጓጓዝ ላይ እንደኾኑም ገልጸዋል። የፕሮጀክቱ አጠቃላይ አፈጻጸም ከ55 በመቶ በላይ መድረሱንም ገልጸዋል። የዋና ማሽነሪዎች ምርት ስለተጠናቀቀ ማሽኖቹ ሲገቡ አፈጻጸሙ በአጭር ጊዜ ከፍ ይላል ነው ያሉት።
‎ፕሮጀክቱን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሠራ እንደኾነም አንስተዋል። ፋብሪካው በዓመት 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ቶን ስሚንቶ የማምረት አቅም እንዳለውም ገልጸዋል። ይህ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ለክልሉ እና ለሀገሪቱ ከፍተኛ የኢኮኖሚ አቅም እንደሚኾንም ይጠበቃል።
‎የምሥራቅ ጎጃም ዞና ዋና አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ በ2018 በጀት ዓመት ባለፉት ዓመታት በጸጥታ ችግር ምክንያት ከሥራ ተስተጓጉለው የነበሩ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ሥራ የመመለስ ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል። አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች ወደ ዞኑ እንዲገቡ መደረጉንም ተናግረዋል።
‎በግንባታ ላይ የሚገኙ ፋብሪካዎችም ወደ ሥራ እንዲገቡ ድጋፍ እና ክትትል እየተደረገ ነው ብለዋል። በዞኑ በተለያዩ አካባቢዎች በርከት ያሉት ኢንዱስትሪዎች አሉ ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው ከነበሩበት ችግር እየወጡ ወደ ተሻለ ሥራ እየመጡ መኾናቸውን አንስተዋል።
‎በዞኑ ኢንቨስትመንት እየተነቃቃ እንደኾነም ገልጸዋል። የዓባይ ጎርጅ እና በአካባቢው ከፍተኛ የማዕድን ሃብት አለ ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው ማዕድንን መነሻ ያደረጉ ኢንዱስትሪዎች በዞኑ አሉ፤ ከዚህ የተሻለ እንዲኖር እንሠራለን ነው ያሉት።
‎ባለፉት ዓመታት የነበሩ መልካም ተሞክሮዎችን በማሳደግ እና የበለጠ በመቀመር የኢንዱስትሪ ዘርፉን የበለጠ ለማሳደግ እየሠራን ነው ብለዋል። በጸጥታ ችግር ምክንያት አካባቢውን ለቅቀው የነበሩ ባለሃብቶች እንዲመለሱ፣ ሌሎች አዳዲስ ባለሃብቶችም ወደ አካባቢው መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ እየተደረገ ነው ብለዋል። ትልልቅ ኢንቨስትመንቶች እየመጡ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
‎ባለፉት ዓመታት የነበረው የጸጥታ ችግር ጉዳት ማድረሱን የተናገሩት ዋና አሥተዳዳሪው በተሠራው የሕግ ማስከበር እና ውይይት የዞኑ የሰላም ሁኔታ መሻሻሉን ገልጸዋል። የተገኘውን ሰላም የበለጠ ለማስፋት እና አስተማማኝ ሰላም ለመገንባት በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።
‎የተፈጠረው ሰላም የተሻለ የልማት እንቅስቃሴ እንዲኖር እያደረገ መኾኑንም ተናግረዋል። በ2019 በጀት ዓመት አዲስ የኢንዱስትሪ ንቅናቄ እንዲኖር እና የኢንቨስትመንት ፍሰቱ እንዲጨምር እንሠራለን ብለዋል። ለኢንቨስትመንት ፍሰቱ መሠረት የኾነውን ሰላምን ደግሞ በአግባቡ እንጠብቃለን ብለዋል።
‎ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
‎የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleመሪዎች በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ አሳሰቡ።
Next articleየማኛ ጤፍ ማቀነባበሪያ እና ሌሎች ኢንዱስትሪዎች ለደብረማርቆስ ማበብ ዐይን ገላጮች ናቸው።