መሪዎች በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ አሳሰቡ።

4
‎የምሥራቅ ጎጃም ዞን እና የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር “አርቆ ማየት፣ አልቆ መሥራት” በሚል መሪ መልዕክት የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ግምግማ እና የ2019 በጀት ዓመት የዕቅድ ትውውቅ መድረክ አካሂደዋል።
‎በመድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ አርቆ በማየት ነገን መመልከት፣ ዛሬ ደግሞ ለነገ መዳረሻችን አልቀን መሥራት አለብን ብለዋል። ‎ርእሰ መሥተዳድሩ የጋራ አላማችን ላይ ለመድረስ ዕቅድ ወሳኝ ነው ብለዋል።
‎ለዚህም የመፈጸም አቅምን ማሳደግ ያስፈልጋል ብለዋል። ለዛሬ ብቻ ሳይኾን ለነገም አቅም የሚኾን ሥራ መሥራት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ተናግረዋል።
‎ዘመናዊ ግብርና ላይ አተኩረን መሥራት አለብን ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ አርሶ አደሮች ቴክኖሎጂ እንዲለማመዱ፣ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ምርት እንዲያመርቱ፣ ከዕለት ፍጆታ ያለፈ ምርት እንዲመረት የሚያደርግ መሪ ያስፈልጋል ብለዋል።
‎መሪዎች ገቢን በአግባቡ እንዲሰበስቡም አስገንዝበዋል። የጤና ተቋማትን፣ ትምህርት ቤቶችን እና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን መገንባት እና በአግባቡ መምራት እንደሚገባ ነው የገለጹት። ተማሪዎች እንዲማሩ ማድረግ አለብን፣ ሰው ሳናስተምር ሀገር ማልማት አንችልም ብለዋል።
‎ሙስና እና ሕገ ወጥነትን መከላከል እንደሚገባም አሳስበዋል። የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎትን ማስፋት ትኩረት እንዲሰጥ አስገንዝበዋል።
ሰላምን መጠበቅ እና አሁን ያለውን ሰላም የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባ ነው ያመላከቱት። የጸጥታ ኃይሉን የበለጠ ማገዝ እና ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ ላይ እንዲሠራ ተናግረዋል።
‎መሪዎች በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል።
‎ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
‎የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleሳዲቅ አምባ – የስሜን ተራራዎች ጫፍ ታሪካዊ ገዳም
Next article‎ከስጋት ወደ ልማት – የምሥራቅ ጎጃም ዞን አዲስ የኢንቨስትመንት ምዕራፍ