ሳዲቅ አምባ – የስሜን ተራራዎች ጫፍ ታሪካዊ ገዳም

9
የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክን የገደል ማሚቶ ተከትሎ፤ የጭላዳ ዝንጀሮዎችን ትርምስምስ አቋርጦ፤ ቁልቁል ሲወረዱ በደመና የተከበበ አንድ ምስጢራዊ ዓለም ይገኛል፤ ታሪካዊው የሳዲቅ አምባ ገዳም።
ገዳሙ እጅግ አስፈሪ በኾነ የገደል ጫፍ ላይ የተመሠረተ እና እጅግ አስፈሪ አንድ መግቢያ በር ብቻ ያለው መኾኑ ወደ ገዳሙ ለመድረስ በሕይወት እና በሞት መካከል ማለፍ ግድ የሚል አድርጎታል።
ወደዚህ ጥንታዊ ገዳም ለመድረስ በስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ ከሚገኘው የስሜን ሎጅ በመነሳት ለአምስት ሰዓታት ያህል ዳገት እና ቁልቁለቱን በእግር አቆራርጦ መጓዝ ግድ ይላል። ይህም ለጉዞ ፈታኝ ከኾኑ የኢትዮጵያ ጥንታዊ ገዳማት መካከል አንዱ አድርጎታል።
ወደ ሥፍራው የሚጓዝ ጎብኝ ከማዶ ኾኖ በገዳሙ አቅራቢያ አስገራሚ ትዕይንትን ይመለከታል። ነጭ የደረቡ ካህናት እና ቢጫ የለበሱ መነኮሳት አንዳችም ፍርሃት ሳያድርባቸው ያንን አስፈሪ ጠባብ የገደል ጫፍ እንደ ድልድይ እየተጠቀሙበት ሲመላለሱ ማየት ለተጓዥ ጉልበት ይሰጣል።
የታሪክ ድርሳናት እንደሚጠቁሙት የሳዲቅ አምባ ገዳም መሠረት የተጣለው በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማለትም በ1640ዎቹ አካባቢ ነው።
በዘመኑ የነበሩ አባ ወልደ ሳዲቅ የተባሉ መናኝ የቤተክርስቲያኑን የወርቅ መስቀሎች፣ የብራና መጻሕፍት እና ክቡራን ንዋያተ ቅድሳትን ከጦርነት ወረራ ለመታደግ ሲሉ ማንም ሊደርስበት የማይችል አስፈሪ አምባ ሲፈልጉ ይህንን ሥፍራ አገኙ። ከዚያም ቅርሶቹን በዚህ አምባ ላይ በመደበቅ ገዳሙን እንደመሠረቱት ይነገራል። ቦታውም “ሳዲቅ አምባ” ተብሎ በስማቸው እንደተሰየመ ነው የሚነገረው።
ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ሳዲቅ አምባ ለዘመናት የጥንታውያን ቅርሶች እና ምስጢራት ማከማቻ ኾኗል። በቤተ መቅደሱ ውስጥ የሚገኙት ቅርሶች እና የውስጥ የግድግዳ ላይ ሥዕሎች ደግሞ የጥንቱን የኢትዮጵያ የሥዕል ጥበብ እንደሚያሳዩ ይነሳል።
ገዳሙ የሚገኝበት ቦታ አስቸጋሪ መኾኑን ተከትሎ ለዘመናት ወደገዳሙ መድረስ እንደማይቻል ይታመን ነበር። በጊዜ ሂደት ግን የውጭ ሀገር ዜጎች ሳይቀሩ ገዳሙን ለመጎብኘት ወደሥፍራው ማምራት እንደቻሉ ተገልጿል። ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሥፍራው ብቻውን በመውረድ ታሪክ የሠራው ጭላዳ ዝንጀሮዎች ላይ ጥናት ያደርግ የነበረው የዱር እንስሳት ባዮሎጂስቱ ቻድ ሀንተር የተባለ የውጭ ዜጋ መኾኑ ይነገራል።
ዛሬ ላይ ይህ ሥፍራ የጀብድ ጉዞ ለሚወዱ የዓለም ጎብኝዎች ተመራጭ መዳረሻ እየኾነ መጥቷል ተብሏል። መንገዱ በማስተካከል ተጓዦች ጉዳት እንዳይደርስባቸው የማድረግ እና የተለያዩ ጥገናዎችን በማድረግ ገዳሙን የመንከባከብ ሥራ መከናወኑ ተገልጿል።
ከወትሮው አኳያ በአሁኑ ወቅት የቱሪስት ፍሰቱ እየጨመረ መኾኑም ተመላክቷል።
ቅርሶችን በመጠበቅ፤ በውስጡ ያሉትን ጥንታዊ የግድግዳ ላይ ሥዕሎችን የመንከባከብ እና ይበልጥ የማስተዋወቅ ሥራ ከሚመለከታቸው አካላት እንደሚጠበቅ ተነግሯል።
ወደሳዲቅ አምባ ገዳም ይምጡ፤ የታሪክ ምስጢርን ይግለጡ !
በመረጃ ምንጭነት የስሜን ሎጂ ይፋዊ ድረ ገጽን፤ ገድለ ወልደ ሳዲቅን እና ሌሎችንም ተጠቅመናል።
ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleእንደዋዛ የሚሰራጩ የጥላቻ ንግግሮች ግን….?
Next articleመሪዎች በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ አሳሰቡ።