
ባሕር ዳር: መስከረም 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የጥላቻ ንግግር የመናገር ነፃነትን ሽፋን በማድረግ በሕዝቦች መካከል አደገኛ የጽንፈኝነት እሳትን የሚያቀጣጥል ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (UN) እንደሚያስቀምጠው የጥላቻ ንግግር ማለት አንድን ግለሰብ ወይም ቡድን በማንነቱ (በብሔሩ፣ በሃይማኖቱ፣ በጾታው ወይም በስደተኝነት ደረጃው) ምክንያት ሰብአዊ ክብሩን የሚያዋርድ፣ የሚያንቋሽሽ፣ የሚያገልል እና ለጥቃት የሚያጋልጥ ማንኛውም የመልዕክት ልውውጥ ነው።
አንድ መልእክት “የጥላቻ ንግግር” ለመባል ሦስት መሠረታዊ መገለጫዎች አሉት።
#የመልዕክቱ ዓይነት፦ በንግግር፣ በጽሑፍ፣ በምስል፣ በሚም (memes) ወይም በምልክት (በአካልም ኾነ በሶሻል ሚዲያ) የተላለፈ፤
#የቃላቱ ይዘት፦ በጥላቻ፣ በንቀት፣ ሰውን ዝቅ በማድረግ ወይም አድልዎን በማንጸባረቅ የተሞላ፤
#የጥቃቱ ዒላማ፦ ትኩረቱ በድርጊት ላይ ሳይኾን በማንነት (በብሔር/በሃይማኖት) ላይ የኾነ፦ይህ ማለት ትችት የሚሰነዘረው ሰውየው በሠራው ስህተት ወይንም ሥራ ላይ ሳይኾን በተወለደበት ብሔር ወይም በሚከተለው ሃይማኖት ላይ ከኾነ እንደማለት ነው።
ይህ አካሄድ የሕዝቦችን አብሮነት በማፍረስ ወደ ከፋ እልቂት ይመራል።
ለዚህም እ.ኤ.አ. በ1990ዎቹ (የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ከተበታተነች በኋላ) የቦስኒያ መሪዎች
የፈጸሙትን ድርጊት በማሳያነት ማንሳት ይቻላል።
መሪዎቹ በሙስሊሞች ላይ
“አሸባሪዎች እና ሥጋቶች” አድርጎ የሚያቀርብ የታቀደ የጥላቻ ንግግር እና የጽንፈኝነት ቅስቀሳ አካሄዱ። በዚህ ምክንያት ከ8 ሺህ 300 በላይ ሙስሊሞች እንዲጨፈጨፉ እና ከ20 ሺህ በላይ እንዲፈናቀሉ አድርጓል።
እንደ ኢትዮጵያ ባለች በብዙ ብሔሮች እና ሃይማኖቶች ባሉባት ሀገር ደግሞ የጥላቻ ንግግር፦
#ማኅበራዊ ውልን ያፈርሳል፦ እንደ ኢትዮጵያ ባለች በብዙ ብሔሮች፣ ሃይማኖቶችና ባሕሎች በተገነባች ሀገር ውስጥ የጥላቻ ንግግር የማኅበረሰቡን የአብሮነት መሠረት ያናጋል።
#ለዘመናት የኖረውን የጋራ መከባበር እና አብሮ የመኖር እሴት በማጥፋት በዜጎች መካከል ፍርሃት እና አለመተማመን እንዲነግስ ምክኒያት ያደርጋል።
#ጥቃቅን ልዩነቶችን እና ታሪካዊ ቅሬታዎችን በማጋነን ከቃላት ማልፎ ወደ ብሔር እና ሃይማኖት ግጭት፣ የሕይወት ሕልፈት እንዲኹም የንብረት ውድመት ያመራል።
#ሰዎች በብሔራቸው ወይም በሃይማኖታቸው ብቻ ሥጋት ስለሚደቅንባቸው እንዲፈናቀሉ እና ለከፋ የሰብአዊ መብት ውድቀት እንዲዳረጉ ያደርጋል።
#የሕግ የበላይነትን እና የመንግሥት ተቋማትን አቅም በማዳከም ሀገሪቱን ወደ ከፋ ሥርዓት-አልበኝነት ይከታል።
#ስለዚህ በግለሰቦችም ኾነ በቡድን የሚሰነዘሩ የጥላቻ ንግግሮች በጊዜ መታረም አለባቸው። አጥፊዎችም መወገዝም መጠየቅም ይኖርባቸዋል።
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይኹኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
