
በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባንጃ ወረዳ በሚገኘው የአስኩና ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለሚማሩ ተማሪዎች የአካባቢው ተወላጆች ያሰባሰቡትን የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል።
የድጋፉ አስተባባሪ አቶ ቦጋለ አይናለም እንዳስታወቁት ቁሳቁሱ ማኅበራዊ ሚዲያን ለበጎ ዓላማ በመጠቀም ከተሰበሰበ ከ160 ሺህ ብር በላይ ወጭ የተገዛ ነው።
በዚህም ለ300 በላይ ተማሪዎች የሚኾን 270 ደርዘን ደብተር እና ሌሎች አስፈላጊ የትምህርት ቁሳቁሶች ለተማሪዎቹ ማደል ተችሏል።
አስተባባሪው አክለውም ከዚህ ቀደም ቤተ መጽሐፍትን በማደራጀት፣ ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ተማሪዎችን በማበረታታት እና በትምህርት ቤቱ ግንባታ የአካባቢው ተወላጆች ንቁ ተሳትፎ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
የባንጃ ወረዳ አሥተዳዳሪ ፀሐይነህ ቦጋለ በበኩላቸው የተደረገው ድጋፍ ደብተር እና እስክርቢቶ ከመስጠት ባለፈ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ሂደት ውስጥ ልዩ ትርጉም ያለው መኾኑን ተናግረዋል።
ድጋፉ ተማሪዎች በቁሳቁስ እጥረት ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው እንዳይሰናከሉ የሚያደርግ እና የወላጆችንም ጭንቀት የሚያቀል መኾኑን አብራርተዋል።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ደስታው አለሙ በትምህርት ዘርፉ የማኅበረሰቡ አጋርነት እየተጠናከረ መምጣቱን ጠቁመዋል።
በዞኑ በክረምት ወቅት ከበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች፣ ከአካባቢ ተወላጆች፣ ከመንግሥት እና ከግል ተቋማት በተደረገ የተቀናጀ ጥረት ከ45 ሺህ ደርዘን በላይ ደብተር እና ልዩ ልዩ ቁሳቁሶችን ማሠባሠብ መቻሉንም ገልጸዋል።
የድጋፉ ተጠቃሚ የኾኑ ተማሪዎች የተደረገላቸው ድጋፍ የእነሱንም ኾነ የወላጆቻቸውን የኢኮኖሚ ስጋት እንደቀረፈላቸው ገልጸው በጥሩ ሥነ-ልቦና ጠንክረው በመማር የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
#አሚኮ #ትምህርት #አዊ #አማራ_ክልል
#ኢትዮጵያ🇪🇹
#እንጅባራ #መስከረም_06_2019_ዓ_ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
