
አማራ ክልልን ከገጠመው የግጭት አዙሪት በማውጣት ወደ ዘላቂ ሰላም ለመመለስ ባለፉት ዓመታት በመንግሥት በኩል ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪዎች ተደርገዋል። የሕዝብ ውይይቶች እና ልዩነቶችን በድርድር የመፍታት ጥረትም የክልሉ ሰላም ምሰሶዎች ኾነው ተሠርቶባቸዋል።
እውነተኛ እና ዘላቂ ሰላም ሊመጣ የሚችለው በጠመንጃ ኀይል ሳይኾን በራሱ ከሕዝቡ የነቃ ተሳትፎ፣ መግባባት እና የሃሳብ ልውውጥ ነው። ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከሃይማኖት አባቶች እና ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር የተደረጉ የሰላም ውይይቶች በክልሉ የተሻለ ሰላም እንዲሰፍን ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አስተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር) ተናግረዋል።
ውይይቶች ማኅበረሰቡ የቆዩ ቅሬታዎቹን በግልጽ እንዲያወጣ በማድረግ የተበላሸውን የመተማመን መንፈስ መልሶ በመገንባት ትልቅ መሠረት እየጣሉ ይገኛሉ። እነዚህ ውይይቶች በርካታ ታጣቂ ኅይሎች በሃሳብ የበላይነት እምነት እንዲኖራቸው አድርጓል። ይህ ሕዝብን ያስቀደመ አካሄድ አሁንም ተጠናክሮ ቀጥሏል።
ከሰሞኑ በሰሜን ጎንደር እና በምዕራብ ጎንደር ዞኖች በርካታ ታጣቂዎች የሰላምን አማራጭ በመቀበል ለሕዝባቸው አለኝታነታቸውን እያረጋገጡ ነው። ይህም ለክልሉ አጠቃላይ ሰላም መስፈን እንደ አንድ ትልቅ ማሳያ እና የተስፋ ኾኗል።
አሁናዊ የሰላም መቀበል ክስተቱ ጦርነት እና የትጥቅ ግጭት የሕዝብን መሠረታዊ ጥያቄዎች ሊመልስ እንደማይችል የጋራ ግንዛቤ መፈጠሩን የሚያሳይ ነው። ሌሎች በግጭት ውስጥ ያሉ አካባቢዎችም ተመሳሳይ የሰላም እርምጃዎችን እንዲከተሉ አርዓያነት ያለው ተግባር ኾኖ ይነሳል።
የሰላም አማራጭን የተቀበሉ ኅይሎች መሣሪያቸውን አስቀምጠው ወደ ማኅበረሰባቸው ሲመለሱ፣ የፈረሱ መሠረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት እና የተስተጓጎሉ ማኅበራዊ አገልግሎቶችን በፍጥነት ለማስጀመር ትልቅ አቅም ፈጥሯል።
የአማራ ክልልን ሰላም ወደነበረበት ለመመለስ መውጫ መንገዱ ሰላማዊ የትግል መንገድ መኾኑንም ተናግረዋል። የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ ሊያገኙ የሚችሉት ሕጋዊ እና ዴሞክራሲያዊ በኾነ መንገድ እንጂ በትርምስ እና በግጭት እንዳልኾነ ገልጸዋል።
ጥፋት እና ውድመት የሕዝቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ወደ ኋላ የሚመልስ ስለመኾኑም አስገንዝበዋል። ልዩነቶችን በሠለጠነ መንገድ በውይይት መፍታት ብቸኛው እና የመጨረሻው አማራጭ እንደኾነም ገልጸዋል።
የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ለሚመጡ ኀይሎችም መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ፣ ምኅረት እና የማቋቋም ሥራ እየሠራ ነው። ከአሁን ቀደም በተለያዩ አካባቢዎች የሰላም አማራጭን የተቀበሉ ታጣቂዎችም በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ተሰማርተው ራሳቸውን እየለወጡ ለሀገርም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው።
መንግሥት ልዩነቶችን በሰላማዊ አማራጭ ለመቋጨት ያለው አቋም በመሬት ላይ ከሚታየው ሰሞናዊ የሰላም መቀበል እርምጃ ጋር ተዳምሮ ሕዝቡ በሰላም ግንባታው ሂደት ላይ በባለቤትነት እንዲሳተፍ ከፍተኛ መነሳሳትን ፈጥሯል።
በአጠቃላይ ባለፉት ዓመታት የተደረጉት የሰላም ጥሪዎች እና የውይይት መድረኮች የአማራ ክልል ወደ ቀድሞው የሰላም እና የልማት ሀዲዱ እንዲመለስ ጠንካራ መሠረትን እየጣለ ነው።
#አሚኮ #ሰላም #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ🇪🇹
#ባሕር_ዳር #መስከረም_06_2019_ዓ_ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
