
ያለፉት ሦስት ዓመታት በኢትዮጵያ በተለይም በአማራ ክልል ፈታኝ የጸጥታ ቀውሶች የታዩባቸው ናቸው። ጦርነት እና ግጭት ማኅበራዊ ትስስርን ያላላበት፣ የዜጎችን የዕለት ተዕለት ኑሮ ክፉኛ ያናጉባቸው ጊዜያት ኾነው ይታወሳሉ።
የሕዝቡ የአዲስ ዓመት ተቀዳሚ ፍላጎት እና የጋራ ምኞትም የጥይት ድምፅ የሚቆምበት እና መረጋጋት የሚሰፍንበት የሰላም ትንፋሽን ማግኘት ነው።
በአነስተኛ የሕጻናት ልብስ ንግድ ሥራ የሚተዳደሩት የቡሬ ከተማ ነዋሪዋ “ዘንድሮስ ሠላም በኾነልን፤ ከምንወዳቸው ሰዎቻችን ጋር ብንገናኝ፤ ሥራችንን ሠርተን የሚገባንን ባገኘን” ሲሉ የሠላም ተስፋቸውን ተናግረዋል።
ግለሰቧ አሁን ያለው የሠላም ሁኔታ የተሻለ መኾኑን ጠቁመዋል። ነገር ግን አስተማማኝ ሠላም የኹሉም መሠረት እንደኾነ ነው የገለጹት። ሕዝብ ሠላም መፈለግ ብቻ ሳይኾን መንግሥት ሠላምን ለማሥፈን በሚያደርገው ጥረት ኹሉ ከጎኑ እንደሚቆም “እኔ አብነት ነኝ” በማለት የሠላም ዘብነታቸውን አረጋግጠዋል።
የመንግሥት መሪዎችም የሕዝቡ ከቀውስ ወደተሟላ ሰላም የመሸጋገር ፍላጎት ቀዳሚ አጀንዳ ኾኖ እንደሚሠራበት በአዲስ ዓመት የመልካም መልዕክታቸው አረጋግጠዋል። የትኛውም ዓይነት የትጥቅ ትግል የሰውን ሕይወት ከመቅጠፍ እና ሀገርን ከማውደም የዘለለ ትርፍ እንደሌለው ባለፉት ዓመታት የነበሩ አካሄዶች ህያው ምስክር ናቸው።
የሕዝብ ጥያቄዎች ሊመለሱ እና ዘላቂ ልማት ሊረጋገጥ የሚችለው ሠላም ሲኖር ብቻ እንደኾ መንግሥት በጽኑ ያምናል፤ ይህንን በሩን ለሠላማዊ ውይይት ክፍት በማድረግ ብዙዎችን ወደ ሰሠማዊ የትግል ምህዳር ስቧቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በ2019 አዲስ ዓመት መልእክታቸው የፖለቲካ ልዩነቶችን በጦርነት ሳይኾን በሠላማዊ ውይይትና ድርድር መፍታት እንደሚገባ ተናግረዋል። ይህንንም የውይይት ባሕል ሥር እንዲሰድ ለማድረግ በሀገራዊ የምክክር ሒደቱ ተግባራዊ ጥረት መደረጉን ነው ያስገነዘቡት።
በአማራ ክልልም ያጋጠሙትን ሳንካዎች በሙሉ በመሻገር፣ ዘላቂ ሠላምን በማጽናት፣ አብሮነትን እና ትብብርን በማጠናከር የተሻለ ዘመን ለመፍጠር እንደሚሠራ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በአዱስ ዓመት የመልካም ምኞት መልዕክታቸው አስገንዝበዋል።
የሠላም ተስፋው መሬት ወርዶ እውን እንዲኾን ግን ሁሉም ወገን የሕዝብን የሰላም ፍላጎት እና ተስፋ ታሳቢ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ሕዝቡ የአዲስ ዓመት ስጦታ አድርጎ የሚጠብቀው የሰላም ቃላትን ብቻ ሳይኾን በተግባር የሚረጋገጥ እውነተኛ ሰላምን ነው።
ዘጋቢ:- ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
