18ተኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ ለኢትዮጵያ ያለውን ድጋፍ ያሳየባቸው ጉዳዮች ምንድን ናቸው ?

9
‎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እና ልዑካቸው ከመስከረም 2/2019ዓ.ም ጀምሮ በተካሔደው 18ተኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ ላይ መሳተፋቸው ይታወሳል።
‎ መስከረም 3/2019 ዓ.ም የጉባዔው ሁለተኛ ቀን ‘‘ጽናትን፣ ፈጠራን፣ ትብብርን እና ዘላቂነትን መገንባት’’ በሚል መሪ መልዕክት የብሪክስ አባል፣ አጋር ሀገራት መሪዎች እና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች በተሳተፉበት ተካሂዷል። ጥምረቱ 140 የጋራ አቋሞችን የያዘ (የኒው ዴልሂ መግለጫ) በማውጣትም የመሪዎቹ ጉባኤ ተጠናቅቋል።
‎የብሪክስ ኒው ዴልሂ የአቋም መግለጫ የዓለም አቀፍ አሥተዳደር ማሻሻያ፣ ዓለም አቀፍ እና ቀጣናዊ ሰላም፣ ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የሕዝብ ለሕዝብ ትሥሥርን ያካተቱ ዐበይት ጉዳዮች ላይ የአባል ሀገራቱን የጋራ አቋም ያንጸባረቀ ነው። ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉን የንግድ ድርጅት ለመቀላቀል የምታደርገውን ጥረት ጥምረቱ በጽኑ እንደሚደግፍ በድጋሚ አረጋግጧል።
በዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ምክር ቤት ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት ብቸኛ እጩ በመኾን ተጨማሪ መቀመጫ እንድታገኝ የሚደረገውን ጥረት በጽኑ እንደሚደግፍም አመላክቷል።
ሀገሪቱ የዓለም አቀፉን የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ኮፕ 32 ለማዘጋጀት የጀመረችውን ተነሳሽነት እና ዝግጅት እንደሚደግፉ በጋራ መግለጫቸው አረጋግጠዋል። ጥምረቱ 19ኛውን የብሪክስ ጉባኤ በቻይና አስተባባሪነት እንዲዘጋጅም በጋራ አጽድቋል።
‎ከመሪዎቹ ጉባኤ ጎን ለጎን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ.ር) ከአባል እና አጋር ሀገራት መሪዎች ጋር በሁለትዮሽ የሀገራቱ ትብብር ዙሪያ ፍሬያማ ውይይቶችን አካሂደዋል። በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በመከላከያ መስኮች ትብብር፣ በዲጂታላይዜሽን ዙሪያ ሊኖሩ ስለሚችሉ ትብብሮች በጥልቀት ተወያይተዋል።
‎በድኅረ ጉባኤ ለመሪዎች በተደረገው የእራት ግብዣ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከተለያዩ የብሪክስ አባል እና አጋር ሀገራት መሪዎች ጋር ታድመዋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው የሁለት ቀናት የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤን አጠናቅቀው ተመልሰዋል።
Previous articleጠላት ጋር አንሠራም፤ የሕዝብን ስቃይም አናራዝምም