
በሰሜን ጎንደር ዞን በጫካ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች ግጭቱ የሀገርን ኢኮኖሚ የሚጎዳ፤ የሕዝብን ሰቆቃ የሚያራዝም መኾኑን በመረዳት የሰላም አማራጭን መቀበላቸውን ተናግረዋል።
የትጥቅ ትግሉ ከታሪካዊ ጠላቶች ጋር ጥምረት በመፍጠር የግለሰቦችን ጥቅም ለማስከበር የሚደረግ፤ በታጣቂዎች መካከል የእርስ በእርስ ግጭት የጎላበት እና ዓላማ የሌለው መኾኑንም አንስተዋል።
በቀጣይ ሰላምን ለማጽናት እና በጫካ የሚገኙ ታጣቂዎች የሰላምን አማራጭ እንዲቀበሉ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ ገልጸዋል።
የሰሜን ጎንደር ዞን ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ዳኝነት ሙሉሰው የሰላም አማራጭ የተቀበሉ ታጣቂዎችን መልሶ ለማቋቋም እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
የሰሜን ጎንደር ዞን አሥተዳዳሪ ዲያቆን ሸጋው ውቤ በዞኑ በርካታ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን በመቀበል በቡድን እየገቡ ነው ብለዋል። ተደጋጋሚ ውይይት በማድረግ እስከ ትጥቃቸው የሰላም አማራጭን እንዲቀበሉ ተደርጓል ነው ያሉት።
ዞኑ በሰሜኑ ጦርነት የተጎዳ መኾኑን ያነሱት አሥተዳዳሪው ታጣቂዎች ከታሪካዊ ጠላት ጋር አንሠራም፤ የሕዝብን ስቃይ አናራዝምም በማለት የሰላም አማራጭን መቀበላቸውን ገልጸዋል።
የሰላምን አማራጭ የተቀበሉ የቀድሞ ታጣቂዎች በጫካ የሚገኙ ታጣቂ ኀይሎች የሰላምን አማራጭ እንዲቀበሉ የበኩላቸውን ጥረት እያደረጉ መኾኑንም ገልጸዋል።
የሰላም አማራጭን በማይቀበሉ ታጣቂዎች ላይ ሕግ የማስከበር ተግባሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
