
የ2019 ዓ.ም አዲስ ዓመትን ስንቀበል፣ ለአዲሱ አመት መልካም ምኞትን ሲገልጽ “ዓመቱን የሰላም ያድርግልን” የማይል ሰው እስከ አሁን ድረስ አላጋጠመኝም። ይህ የግል ተዝብቴ ቢኾንም በብዙዎች ዘንድ የሚጋነን ግን አይኾንም።
ብዙ ሰው የሰላም ጉዳይ ያስጨንቀዋል። ያሳለፍነው ዓመትም ከህጻን እስከ አዋቂ፣ ከአርሶ አደር እስከ ምሁር፣ ከተማሪ እስከ የሃይማኖት መሪ ለሁሉም ቀዳሚ እና አገብጋቢው ነገር የሰላም ጉዳይ ኾኗል።
ለዚህም ነው ከግለሰብ እስከ ሃይማኖት እና መንግሥት ተቋማት መሪዎች ድረስ የሰላምን ጉዳይ በአዲስ ዓመት የምኞት መግለጫቸው የሚያነሱት።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ሊቀ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ለ2019 ዓ.ም የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ሲያስተላልፉ ባለፈው ዓመት የተከሰቱት ችግሮች ሁሉ በዓዲሱ አመት እንዳይደገሙ በማድረግ በሀገሪቱ ሰላምን ማስፈን እንደሚገባ አባታዊ ምክራቸውን ገልጸዋል።
ባለፈው ዓመት ያጋጠሙት ችግሮችን ሁሉ በንጹህ ሕሌና በጥልቀት መገምገም ከተቻለ ጥቅሙን እና ጉዳቱን ዳኝነት ለመስጠት እና ውሳኔ ለመወሰን አያስቸግርም ነው ያሉት።
ባለፈው ዓመት በሀገራችን የተከሰቱትን ለሰው ልጅ የማይበጁ ድርጊቶች ሁሉ በአዲሱን ዘመን ፈጽሞ እንዳይቀጥሉ ማድረግ እንደሚያስፈልግ መክረዋል። ለዚህም ሁሉም ሰው ሊወስን ይገባል ነው ያሉት። ይህ ካልኾነ አዲስ ዓመት ሲመጣ “እንኳን አደረሳችሁ” መባባሉ ትርጉም እንደማይኖረውም ነው የጠቆሙት።
“ለሁሉም የሰላም እጦት መድኃኒቱ ቀና አዕምሮ ነው” ያሉት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በአዲሱ ዓመት ቅን እና በጎ በማሰብ ኢትዮጵያ ሰላም የሰፈነበት እንድትኾን ማድረግ እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።
ኢትዮጵያውያን ሁሉ በአንድነት ለሰላም እና ለይቅርታ በመቆም አለመግባባቶችን በሂደት በመፍታት መቀጠል እንደሚገባ መክረዋል።
