በምሥራቅ ጎጃም ዞን የጠመንጃ ላንቃ እየተዘጋ፣ የሕዝብ እፎይታ እና የልማት ቱሩፋት መልኮች እየተገለጡ ነው።

7
🕊️
የምሥራቅ ጎጃም ዞን አሥተዳደር ከማኅበረሰቡ እና ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በተደረገ ቅንጅታዊ አሠራር የሰላሙ ሁኔታ በእጅጉ እየተሻሻለ መምጣቱን አስታውቋል።
በዞኑ ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች እንደገለጹት ካለፉት ሦስት ዓመታት አስቸጋሪ ሁኔታዎች በተሻለ መልኩ አንጻራዊ ሰላም እና ለውጦች መታየታቸውን ነግረውናል። ቀደም ሲል ከነበረው ውጥረት እና የጸጥታ ችግር አንጻር አሁን ላይ ማኅበረሰቡ ከፍርሃት ወጥቶ በነጻነት በመንቀሳቀስ የዕለት ከዕለት ተግባራትን እያከናወነ መኾኑን ነው ነዋሪዎቹ የገለጹት።
በተለይም ከአሁን በፊት በብዙ አካባቢዎች ተቋርጦ የነበረው የመማር ማስተማር ተግባር ወደ መደበኛ የማስተማር ሥራ ለመመለስም ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል። ይህም ለማኅበረሰቡ ትልቅ እፎይታ የሚሰጥ እንደኾነ ነው የገለጹት። የሁሉንም አካባቢዎች ሰላም ለማጽናት እና የሕዝቡን ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሰላም ጉዳይ ከዚህም በላይ መጠናከር እንዳለበትም ጠቁመዋል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ የዞኑ ሰላም እየተሻሻለ በመምጣቱ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች በተገቢው እየተከናወኑ ነው ብለዋል። በዚህም ለውጦች እየተመዘገቡ እንደኾነ ነው የተናገሩት።
ከዚህ በፊት የጸጥታ ስጋት የነበሩ አካባቢዎች አንጻራዊ ሰላም በመረጋገጡ ባለሙያዎች እስከ ቀበሌ ድረስ በመውረድ ድጋፍ እያደረጉ መኾኑንም ጠቁመዋል። በሰላም ግንባታ ዙሪያ በተከናወኑ የቅንጅት ሥራዎች በርካታ አካላት የሰላም አማራጭን እየተከተሉ እንደሚገኙም አንስተዋል።
የሰላም አማራጭን ለተቀበሉ አካላትም የተሐድሶ ሥልጠና ተሰጥቷል ብለዋል። በተለያዩ የሥራ መስኮች በመሰማራት የተረጋጋ ሕይወት እንዲመሩ ተደርጓል ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው የተለያዩ ዕድሎችን የማመቻቸት ሥራ እየተከናወነ መኾኑንም ነው የገለጹት።
ማኅበረሰቡ የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም በመጠቀም የዕለት ከዕለት ሕይወቱን በሰላም እየመራ ይገኛል ነው ያሉት። በቀጣይም ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ እና የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ከጸጥታ ኃይሉ እና ከሕዝቡ ጋር በቅንጅት መሥራት ይገባል ብለዋል።
አሁንም የሰላም በሩ ክፍት በመኾኑ ሌሎችም የታጠቁ አካላት የሰላም አማራጩን በመቀበል የተረጋጋ ሕይወት እንዲመሩ ጥሪ አቅርበዋል።
#ሰላም #peace # ኢትዮጵያ🇪🇹
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየአዲስ ዓመት ጎህ – ተናፋቂው የሠላም ፀዳል