“መስከረም” የምድር እፎይታ፣ የሰው ልጅ አዲስ ተስፋ”

6
መስከረም የዘመን መባቻ ብቻ አይደለም፤ ምድር ከከባድ ደመና እና ውችንፍር ወጥታ የምትሟሟቅበት፣ የሕይወት እና የሰው ልጅ ተስፋ አዲስ ኅብረ-ቀለም የሚለብስበት የውበት አክሊል እንጂ።
ክረምቱ ሲያከትም፣ የምድር ጥሙ ሲቆረጥና ሰማዩ ሲጠራ፣ የኢትዮጵያ መስከረም ለሰው ልጅ፣ ለእንስሳትና ለአዕዋፋት እኩል የነፃነት እና የእፎይታ ብስራት ይዞ ይመጣል።
ምድሯ በአደይ አበባ ወርቃማ ምንጣፍ ስትሸለም፣ ወንዞች ሲጠሩ፣ የቢራቢሮዎችና የንቦች የደስታ ክንፍ ሲዘረጋ የተፈጥሮና የሰው ልጅ ሕይወት እጅግ በተዋበ መልኩ ይጋባሉ።
ይህ ወር ሀገራዊ ስሜት፣ ባሕላዊ እሴትና መንፈሳዊ ውበት በአንድነት የሚፈተሉበት የፍቅርና የእርቅ መድረክ ነው።
የክረምቱን ድቅድቅ ደመና ገፎ አዲስ ብርሃን የሚረጭበት፣ ህፃናት በአበባ ስዕሎቻቸው ተስፋን በየደጃፉ የሚያበስሩበት፣ የተነፋፈቁ አፍቃሪዎችና የተራራቁ ዘመዶች የሚገናኙበት የህይወት አዲስ ምዕራፍ ነው።
መስከረም ሀገር በባሕላዊ አልባሳት፣ በወርቃማ አደይ አበባ፣ በደመራ እሳትና በምስጋና የምታጌጥበት የነፃነትና የአዲስ ህይወት ተምሳሌት ነው።
ኢትዮጵያዊያን ደራሲያን፣ ባለቅኔዎችና ድምፃውያን የመስከረምን ተፈጥሯዊ ውበት፣ ተስፋና ሀገራዊ መልክ ከኢትዮጵያ ጋር አዋህደው በግጥም፣ በስዕልና በዜማ ገልጸውታል።
በደራሲ በዓሉ ግርማ “መስከረም የብራ፣ የፍቅርና የአዲስ ተስፋ ወር ነው፤ ኢትዮጵያ በክረምት ወራት ተኮማትራ ከቆየችበት የጭጋግና የደመራ ከረጢት ወጥታ፣ ውበቷን፣ ቀለሟንና አየርዋን ለዓለም የምታሳይበት የወራት ንጉሥ ነው፤” ይለናል።
ደራሲና ባለቅኔ ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን
“ኢትዮጵያ ማለት የአደይ አበባ፣ የመስቀል ደመራና የጥቢ ብርሃን መባቻ ነች። መስከረም ደግሞ የዚች ሀገር ታሪክና ተፈጥሮ ተጋብተው የሚያበሩበት የዕንቁጣጣሽ አክሊል ነው።” ብለው ከተበውታል።
ሰዓሊና ባለቅኔ ገብረክርስቶስ ደስታም
“በሽቱ መዓዛህ ለውጠው ዓመቱን፤
ይታደስ ያረጀው ፍጥረት ሌላ ይሁን…” በማለት
መስከረምን እንደ ምድርና የሰው ልጅ መንፈስ ማደሻ አድርጎ ይገልጸዋል።
ድምፃዊት እጅጋየሁ ሽባባው /ጂጂ/
“መስከረም ለምለሙ፣ መስከረም ለምለሙ፤
ብሩህ ዕንቁጣጣሽ ደስታ ለዓለሙ…” በማለት
(የመስከረምን ለምለምነት ከሀገርና ከዓለም ደስታ ጋር በማያያዝ በዜማዋ አስተጋብታዋለች።
በአጠቃላይ መስከረም ወር ኢትዮጵያ እውነተኛ የተፈጥሮ ማንነቷን እና ውበቷን እና ድምቀቷን ለዓለም የምታሳይበት የህይወት፣ የሰላም እና የብሩህ ተስፋ ዘላለማዊ ማህተም ነው።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
Previous articleአስተማማኝ ሰላም ማጽናት ልማቶችን ከዳር ለማድረስ ዋናው መሠረት ነው።
Next articleየጥምር ጦሩ የማድረግ አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል።