
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የ2018 በጀት ዓመት የፓርቲ እና የመንግሥት ሥራዎች አፈጻጸም እና የ2019 በጀት ዓመት እቅድ እየተገመገመ ነው። በመድረኩ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ የሁሉም ወረዳዎች እና ከተማ አስተዳደሮች ከፍተኛ እና መከካለኛ መሪዎች ተሳትፈዋል።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው ያለፈው ዓመት ጥራት ያለው እቅድ በማቀድ፣ ፈፃሚን በማዘጋጀት እና እቅዶችን በመፈጸም ረገድ በልዩ ሁኔታ ርብርብ የተደረገበት እንደነበር ገልጸዋል።
አብዛኛዎቹ ተቋማት እና መሪዎች ተልዕኳቸውን በመወጣት ረገድ አበረታች ሥራ መሥራታቸውንም ተናግረዋል።
በሰብል ምርታማነት፣ በእርሻ ሜካናይዜሽን፣ በእንስሳት ሃብት፣ በገቢ አሰባሰብ፣ በከተሞች ገፅታ ግንባታ እና በሌሎችም ዘርፎች ስኬቶች መመዝገባቸውንም አንስተዋል።
ፅነፈኝነትን በመታገል አብሮነት ገዥ ትርክት እንዲሆን ተሠርቷልም ነው ያሉት።
ለሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ቀጣይነት ዘብ የሚቆም እና ለሕዝቡ ደህንነት የሚተጋ የፀጥታ መዋቅር በመገንባቱ
የብሔረሰብ አሥተዳደሩ የሰላም ሁኔታ መሻሻል ማሳየቱንም ገልጸዋል።
በተለያዩ የልማት፣ የመልካም አስተዳደር እና የፀጥታ ሥራዎች ትግበራ የማኅበረሰብ ተሳትፎ ልህቀት የታየበት እንደነበርም አሥተዳዳሪው አንስተዋል።
በ2018 በጀት ዓመት ታቅደው ያደሩና ለ2019 በጀት ዓመት የታቀዱ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች ከዳር እንዲደርሱ አስተማማኝ ሰላም ማፅናት ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑንም ገልጸዋል።
በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አለሙ ሰውነት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫን ጨምሮ በኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ መስኮች በርካታ ስኬታማ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል። የመሪዎች የማቀድና እቅዶችን የመፈፀም አቅም እያደገ መጥቷልም ብለዋል።
በ2019 በጀት ዓመት የብሔረሰብ አሥተዳደሩን ሕዝብ ተጠቃሚነት ከፍ የሚደርግ የተሻለ እቅድ ታቅዶ ወደ ሥራ ስለመገባቱም አስረድተዋል።
በየደረጃው የሚገኙ መሪዎች ለዕቅዱ ተፈፃሚነት ኅብረተሰቡን በባለቤትነት በማሳተፍ መንቀሳቀስ እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
